በከፍተኛ ሊግ የመወዳደር እድል ያገኘው ወሎ ኮምቦልቻ የቀድሞውን አሰልጣኙ መላኩ አብርሀን መልሶ ቀጥሯል።
በ2010 ውድድር ዓመት በምድብ ሀ ተመድቦ ውድድሩን ሲያከናውን የነበረው ወሎ ኮምበልቻ የውድድሩ መጨረሻ ሳምንት ድረስ ላለመውረድ ሲያደርግ የነበረው ትግል ሳይሳካለት ወደ አንደኛ ሊግ ቢወርድም ከፍተኛ ሊጉ በአዲስ ፎርማት የተሳታፊ ቁጥር ጨምሮ የሚከናወንበት በመሆኑ ሳይወርድ የመቆየት እድል ገጥሞታል።
ከአሰልጣኝ ብርሃኔ ገብረእግዚዓብሔር ጋር የተለያየው ወሎ ኮምቦልቻ በ2007 እና 2008 አሰልጣኙ የነበሩትና በኢትዮጽያ እግርኳስ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን አሰልጣኝ መላኩ አብርሀን (ሻምበል) በሁለት ዓመታት ውል ቀጥሯል። አሰልጣኝ መላኩ በኢትዮጽያ እግር ኳስ በተጫዋችነት፣ በኢንስትራክትነት እንዲሁም በአሰልጣኝነት ከ35 ዓመታት በላይ ያሳለፉ ሲሆን ኒያላ (ሁለት ጊዜ)፣ ዴንዴሪ ሚሲዮናል (ጅቡቲ)፣ ፎር ኢት ሀዋሳ፣ መተሀራ ስኳር፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ (ሁለት ጊዜ)፣ ባህር ዳር ዩንቨርሲቲ፣ ናሽናል ሴሜንት፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ኢትዮጵያ መድን ሲያሰለጥኑ አምና በፋሲል ከነማ ቴክኒክ ዳይሬክተርነት መስራታቸው ይታወሳል።