ለመጀመርያ ጊዜ በስድስት የክልል ቡድኖች መካከል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው መስማት የተሳናቸው የእግርኳስ ፌስቲቫል ለፍፃሜ የሚጫወቱ ቡድኖች ተለይተው ታወቁ ።
በኤፎ አድቨርታይዚንግ አዘጋጅነት ከጥቅምት 20 ጀምሮ በስድስት የክልል ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የቆየው መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ፌስቲቫል ውድድር ዛሬ ጎፋ በሚገኘው የመብራት ሀይል ሜዳ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተካሂደው ሀዋሳ እና ሆሳዕና ለፍፃሜ ዋንጫ ማለፈቸውን አረጋግጠዋል። ጠዋት 03:00 በተካሄደው የሀዋሳ እና የቢሸፍቱ ጨዋታ ሀዋሳ 4 – 3 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ለሀዋሳ የድል ጎሎችን ጌታቸው ጌታሁን (2) ትንሣኤ አበበ (2) ሲያስቆጥሩ የቢሸፍቱን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል ብሩክ ካሳ እና ዮሴፍ አያሌው(2) አሰቆጠረዋል። በዚህ ጨዋታ ከሀዋሳ በኩል ትንሣኤ አበበ ያደረገው እንቅስቃሴ እጅግ አስገራሚ ነበር።
05:00 በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ሰናይን (ከአዲስ አበባ) እና ሆሳዕናን አገናኝቶ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2 – 2 ተጠናቆ በመለያ ምት ሆሳዕና 5 – 4 አሸናፊ ሆኗል። ሰናዮች በፊሊሞን ልዑል እና አባስ ዘይኑ ጎሎች እየመሩ እረፍት ቢወጡም ሆሳዕናዎች ከእረፍት መልስ ተሻሽለው ቀርበው በኤቤሴሎም አበበ እና ሦዩም ዓሉሙ አማካኝነት አቻ ሆነው መደበኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው የመለያ ምት ሆሳዕና 5 – 4 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኗል።
በሆሳዕና እና በሀዋሳ መካከል የሚደረገው የፍፃሜው ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መልካም ፍቃድ ከሆነ እሁድ 08:00 ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ አስቀድሞ የሚደረግ ሲሆን ይህ የማይሳካ ከሆነ ነገ ከጠዋቱ 04:00 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚጠናቀቅ ይሆናል።