ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓዲግራት ዩ. ከ መቐለ 70 እንደርታ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነገ ብቸኛ ጨዋታ የሆነውን የትግራይ ደርቢ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። 

በርካታ ዓመታት ባያስቆጥርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ውጥረት ሲነግስበት የሚታየው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና መቐለ 70 እንደርታ የትግራይ ደርቢ ፍልሚያ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ነገ 09፡00 በመቐለ ይደረጋል። በዚህ ረገድ የሁለቱ ቡድኖች የአምናው የሁለተኛ ዙር ግንኙነት በብዙዎች በመጥፎ ጎኑ የሚነሳ ነበር። የ17ኛ ሳምንቱ ጨዋታ በደጋፊዎች ነውጥ ተቋርጦ ከሁለት ወራት ቆያታ በኋላ ነበር ሁለተኛው አጋማሽ እንዲከናወን የሆነው። በነገው ጨዋታ ባለሜዳ የነበረው ወልዋሎ ዓ.ዩ ቢሆንም የዓዲግራቱ ወልዋሎ ስታድየም ዕድሳት ላይ መሆኑን ተከትሎ ነው መርሀ ግብሩ ወደ መቐለ የዞረው። ወልዋሎ በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታው በሀዋሳ የ3-0 ሰፊ ሽንፈት ሲደርስበት መቐለ 70 እንደርታ በበኩሉ ሜዳው ላይ ደደቢትን 2-0 በመርታት ነበር ውድድሩን የጀመረው። 

ከባለፈው ዓመት የተጫዋቾች ስብስብ እና የቡድን ቅርፅ በተለየ መልኩ የቀረቡት ሁለቱ ክለቦች በነገው ጨዋታ ሁለቱም በተመሳሳይ በመስመር ላይ ያተኮረ የማጥቃት አጨዋወት ይዘው እንደሚገቡ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ በዋነኝነት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ከግብ ጠባቂ ኳስ መስርተው የሚጫወቱት መቐለዎች በኳስ አመሰራረት ሂደት ላይ ከታታሪዎቹ የወልዋሎ ሶስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች የሚገጥማቸው ፈተና ሌላው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል በአብዛኛው የጨዋታ እንቅስቃሴ በተለጠጠ አቋቋም የሚታወቁ የፊት መስመር ተሰላፊዎች እና በጠባብ ቅርፅ የሚጫወት የአማካይ ክፍል የሚጠቀመው ወልዋሎ በመሀል ክፍሉ ግራ እና ቀኝ የሚፈጠረው ሰፊ ክፍተት በመስመር ተከላካዮቹ የተመጣጠነ የማጥቃት ተሳትፎ ቀርፎ ካልገባ በባለፈው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ከነበሩት  የመቐለ የመስመር ተከላካዮች የሚጠብቀው  ፈተና ሌላው በጨዋታው ተጠባቂ ነገር ነው።

በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት የቡድን ስብስባቸው ሳስቶ የነበሩት ወልዋሎዎች በሀዋሳው ጨዋታ አራት ተጠባባቂ ተጫዋቾችን ብቻ ለመጠቀም ተገደው ነበር። በነገው ጨዋታ ግን ቅጣት ላይ የነበሩት እንየው ካሳሁን እና ኤፍሬም አሻሞ እንዲሁም በጉዳት ያልተሰለፉት ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና አብዱርሀማን ፉሰይኒ እንደሚደርሱ ተሰምቷል። ከዚህ በተጨማሪ የስድስት ወር ቅጣት ተላልፎበት የነበረው በረከት አማረበመሆኑም ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ብቁ እንደሚሆን ይጠበቃል።  በወልዋሎ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ዳንኤል አድሀኖም ብቻ ሆኗል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩልም በተመሳሳይ ጉዳት ላይ ይገኙ የነበሩት ስዩም ተስፋዬ ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና ያሬድ ከበደ እንዳገገሙ ታውቋል።

የእርሰ በእርስ ግኑኝነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ወደ ብሄራዊ ሊግ ካደገበት 2005  ጀምሮ ቡድኖቹ በ12 ጨዋታዎች ሲገናኙ መቐለ ሁለቴ ወልዋሎ ደግሞ አንዴ ድል ሲቀናቸው ቀሪዎቹን ዘጠኝ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በ12ቱ ጨዋታዎች መቐለ 70 እንደርታ 9 ግቦች እንዲሁም ወልዋሎ 8 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– በመሸናነፍ በተጠናቀቁት ጨዋታዎች መቐለዎች በ2005 3-2  እና  በ2007 1-0 ሲያሸንፉ ወልዋሎዎች በበኩላቸው ባለፈው ዓመት 1-0 መርታት ችለዋል። 

– ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው መቐለ ላይ 0-0 ሲለያዩ በደጋፊዎች ስርዓት አልበኝነት ተቋርጦ በነበረው የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ወልዋሎ 1-0 አሸንፏል።

– ሁለቱ ክለቦች መቐለ ላይ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ተሸናንፈው አያውቁም። 

ዳኛ 

– በላይ ታደሰ (ኢንተርናሽናል) ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

በረከት አማረ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – በረከት ተሰማ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – አስራት መገርሳ – አፈወርቅ ኃይሉ

አብዱርሀማን ፉሴይኒ- ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፕሪንስ ሰቨሪንሆ                                         

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፔ ኦቮኖ 

ሥዩም ተስፋዬ – ቢያድግልኝ ኤልያስ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ  

ያሬድ ከበደ – ሐይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ 

አማኑኤል ገብረሚካኤል