የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 13 ተጫዋች በመያዝ አመሻሹ ላይ ሱሉልታ በሚገኘው ሜዳ የመጀመርያ ልምምዳቸውን አድርጓል።
በ2020 ቶኪዮ ላይ የሚከናወነው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በእግርኳሱ ዘርፍ ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል ለመገኘት በአፍሪካ ዞን የቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን ከሶማሊያ አቻው ጋር የተመደበው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እየተመራ በቅርቡ ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።
መቀመጫውን ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ያደረገው ቡድኑ ዛሬ አመሻሹ ሱልልታ በሚገኝ ሜዳ ባልተሟላ ሁኔታ 13 ተጫዋች በመያዝ የመጀመርያ ልምምዱን አድርጓል። በልምምዱ ወቅት ግብ ጠባቂዎቹ ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ፅዮን መርዕድ ፣ ምንተስኖት አሎ፤ ተከላካዮቹ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ፍሬዘር ካሳ እና ሸዊት ዮሐንስ፤ አማካዮቹ የዓብስራ ተስፋዬ ፣ አቤል እንዳለ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዳዊት ማሞ እንዲሁም አጥቂዎቹ አቡበከር ሳኒ ፣ ቡልቻ ሹራ እና እስራኤል እሸቱ ሲገኙ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ በረከት ደስታ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ወንድሜነህ ደረጄ በፓስፖርቱ ጉዳይ በልምምዱ ላይ ሳይሳተፉ ቢቀርም ከነገ ጀምሮ ወደ ልምምድ እንደሚመለሱ ሰምተናል። መሣይ ጳውሎስ ፣ ደስታ ደሙ ፣ እንየው ካሳሁን (ተከላካዮች) ሐይደር ሸረፋ፣ በኃይሉ ተሻገር ፣ በረከት ወልዴ ፣ (አማካዮች) ሱራፌል ጌታቸው ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ አቡበከር ነስሮ (አጥቂዎች) ደግሞ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያልተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።
እንደ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ገለፃ ከሆነ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦላቸው ተገኝተው ሪፖርት ባላደረጉት ዘጠኝ ተጫዋቾች ምትክ ሌሎች ተጫዋቾችን እንደሚጠሩ በማያወላዳ መንገድ ተናግረዋል ” የብሔራዊ ቡድን ጥሪ አክብረው በሰዓቱ 17 ተጫዋቾች መጥተዋል። እነሱን ይዘን እየቀጠልን በጎደሉት ምትክ ሌሎች ተጫዋቾችን በመጥራት ዝግጅታችንን እንቀጥላለን።” ብለዋል። ይህ አቋማቸው የሚፀና ከሆነ በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ወቅት እየተንጠባጠቡ በመምጣት በቡድን መንፈስ እና በዝግጅት እቅድ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ ይታመናል። በተጓደሉት ምትክ ሊጠሩ ከሚችሉት መካከልም የሲዳማ ቡናዎቹ ፈቱዲን ጀማል እና ሐብታሙ ገዛኸኝ እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማዎቹ ፍሬው ጌታሁን እና ገናናው ረጋሳ እና ሌሎች ተጫዋቾች ይካተታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታዋን ኅዳር 5 በአዲስ አበባ ስታድየም ኅዳር 10፡00 ላይ ስታደርግ ቱኒዚያዊያኑ ጉሂራት ሃያዜም (ዋና)፣ ራምዚ ሄሪች እና ካሊል ሃሳኒ (ረዳቶች) ፣ ዋሊድ ጀርዲ (አራተኛ ዳኛ) እንዲሁም ሱዳናዊው አሚር ዑስማን ሙሐመድ እና ግብጻዊው ኢሳም አልዲን (ኮሚሽነር እና ታዛቢ) ጨዋታውን እንዲመሩ በካፍ የተመደቡ ናቸው።