አስራት አባተ የቢሾፍቱ ከተማ አሰልጣኝ ሆኗል

ባሳለፍነው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አሳልፎ የነበረው አስራት አባተ የቢሾፍቱ ከተማ አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደሞትነት ከሚጠሩ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው አሰልጣኝ አስራት አባተ። በተለይ በደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በነበረው ቆይታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማፍራት እና ክለቡ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን ማድረግ ችሎ ነበር። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እየመራም ጠንካራ የማጣሪያ ተሳትፎን እንዳደረገ የሚታወስ ነው።

አሰልጣኙ ከ2009 ጀማሮ የአዲስ አበባ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ በመሆን እስከ ውድድሩ አጋማሽ ከቆየ በኃላ የአሰልጣኝ ስዩም ከበደን መልቀቅ ተከትሎ ወደ ወንዶቹ ቡድን ተዘዋውሮ እስከ አምናው የውድድር ዓመት መጨረሻ ሳምንታት ቆይቷል። አሰልጣኝ አስራት ለጥቂት ጊዜያት ከአሰልኝነት ከራቀ በኃላ ከኢትዮጵያ ቡና ረዳት አሰልጣኝነት እና ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ጋር ስሙ ቢያያዝም የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ቢሾፍቱ ከተማን በአንድ ዓመት የውል ስምምነት በአሰልጣኝነት እንደሚመራ ታውቋል።