ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የሁለተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ነገ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎንደር እና መቐለ ላይ የሚከናወኑትን ሁለት የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን።


ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ነገ 09፡00 ላይ በፋሲለደስ ስታድየም የሚደረገው ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለሦስት ዓመታት ከቆዩበት የቀድሞው ክለባቸው ሀዋሳ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል። ወደ ሲዳማ ባደረገው ጉዞ ሽንፈት ገጥሞት የተመለሰው ፋሲል ከነማ በሜዳው በሚያደርገው የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታ እስካሁን ድል አርጎት ከማያውቀው ሀዋሳ ከተማ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደሚፋለም ይጠበቃል። በመጀመርያ ሳምንት ከተደርገጉ ጨዋታዎች ሁሉ በሰፊ የግብ ልዩነት ወልዋሎን የረቱት ሀዋሳዎችም በሊጉ ኮስታራ ተፎካካሪ መሆናቸውን ለማሳየት የአምናውን የሜዳ ውጪ ደካማ አቋማቸውን አስተካክለው ከጎንደር በአሸናፊነት መመለስ አስፈላጊያቸው ይሆናል። 

በጨዋታው የሀዋሳ ከተማ የመስመር እንቅስቃሴ ለአፄዎቹ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል መናገር ይቻላል። በተለይም ደስታ ዮሀንስ በወልዋሎው ጨዋታ ያሳየውን ብቃት መድገም ከቻለ እነደ ሲዳማው አዲስ ግደይ ሁሉ በመስመር በኩል ፋሲሎችን የማስጨነቅ አቅም ይኖረዋል። ዘግይተው ወደ ሳጥን የሚደርሱ የቡድኑ አማካዮችም ከፊት አጥቂዎቹ ውጪ ከመስመር የሚደርሱትን ኳሶች ወደ ውጤት ለመቀየር ተጨማሪ አማራጮች ናቸው። በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት የሚያደርጉት ፋሲሎች ደግሞ በመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ያላስተነገደው ሶሆሆ ሜንሳህን መረብ ለመድፈር የመጨረሻ ኳሶችን ከአማካይ ክፍላቸው የሚጠብቁ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ መሀል ላይ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸውም የመስመር አጥቂዎቻቸው እገዛ አስፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው። የአጥቂያቸው ኢዙ አዙካ በቶሎ ወደ ግብ ማስቆጠሩ መምጣት ለፋሲሎች መልካም ነገር ተደርጎ የሚቆጠር ቢሆንም የተጫዋቹ መጎዳት አሰልጣኝ ውበቱ ቦታውን ለመሸፈን ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ ያደርጋቸዋል። 

የፋሲል ከነማዎቹ ሰለሞን ሀብቴ ፣ ፋሲል አስማማው እና በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኢዙ አዙካ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ታውቋል። ከዚህ ውጪ ለ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተመረጡት ተክለማርያም ሻንቆ እና እስራኤል እሸቱ ከሀዋሳ ጋር አንመለከታቸውም። በአንፃሩ የወረቀት ጉዳዮቹን የጨረሰው የሀዋሳ መስመር ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር በቡድኑ ውስጥ እንደሚካተት ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ፋሲል በ2009 ወደ ሊጉ ካደገ በኋላ በሊጉ ከተኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው ሀዋሳ ከተማ  ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል በነዚህ ግንኙነቶች ሦስት ግቦች ቢያስቆጥርም እስካሁን ድል አልቀናውም። 

– ፋሲል ከነማ ጎንደር ላይ ሀዋሳን ያስተናገደባቸው ሁለት ጨዋታዎች በ 1-1 እና 2-2 ውጤቶች የተጠናቀቁ ነበሩ።  

ዳኛ 

– ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ የሚመራ ይሆናል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ሙጂብ ቃሲም – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ያስር ሙገርዋ – ከድር ኩሊባሊ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኤዲ ቤንጃሚን – አብዱርሀማን ሙባረክ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ –ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን –አዳነ ግርማ – ታፈሰ ሰለሞን – ደስታ ዮሃንስ

ኄኖክ ድልቢ – ገብረመስቀል ዱባለ


ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ቡና

በሊጉ በርካታ ግቦች የሚታዩበት እና አዝናኝ ከሚባሉ ግንኙነቶች አንዱ የሆነው የደደቢት እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በመቐለ ስታድየም ይጀምራል። ሆኖም በአዲስ አበባ ስታድየም ሲታይ የኖረው የቡድኖቹ የወትሮው መመጣጠን ዘንድሮ ይኖራል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ደደቢት በፋይናንስ እጥረት የረጅም ጊዜ ተጫዋቾቹን ለቆ በገነባው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳየው አቋም እና ያጋጠመው ሽንፈት ለዚህ ማሳያ ነው። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡና ይበልጥ ያጠናከሩትን ዝውውሮች ፈፅሞ ከአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ጋር  በተፈተነበት ጨዋታ ድሬዳዋን 2-1 በመርታት ነበር ሊጉን የጀመረው። 

ደደቢት በመቐለው ጨዋታ የአማካዮቹን ቁጥር አራት አድርጎ ጀምሮ አንድ ግብ ካስተናገደ በኋላ ቁጥራቸውን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ የቅርፅ ለውጥ አድርጎ ነበር የጨረሰው። ነገም በታታሪ የመስመር አጥቂዎች የሚታገዘውን የኢትዮጵያ ቡናን አማካይ ክፍል ጫና ለመቋቋም መሀል ክፍል ላይ አምስት ተጫዋቾችን መጠቀም ምርጫው እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረው ደደቢት በዋነኝነት የፊት አጥቂዎቹን መሰረት ያደረግው የማጥቃት መንገዱ ከቡናማዎቹ ፈተና ሊገጥመው የምችልበት ዕድል የሰፋ ነው። የተሻለ ልምድ ያላቸው የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለም አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት በቀላሉ የሚተካ አይደለም። በድሬዳዋው ጨዋታ ሙሉ ብልጫን ማሳካት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተቸገሩበት ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣታቸው በራስ መተማመናቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ዕሙን ነው። ነገር ግን የቡድኑ የአጨዋወት ጉልበት በመሀል ሲወርድ መታየቱ እና የካሉሻ አልሀሰን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንደተጠበቀው አለመሆን ከነገው ጨዋታ በፊት የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን ትኩረት የሚሻ ይመስላል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የመስመር ተከላካዮቹን ተሳታፊ ባደረገ የሁለቱ ኮሪደሮች ጥቃት ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። 

ጉዳት ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች አማኑኤል ዮሀንስ እና ቶማስ ስምረቱ በማገገም ላይ ቢሆኑም ወደ መቐለ ያልተጓዙ ሲሆን የደደቢቶቹ አቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ ደግሞ በ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ጨዋታው ያልፋቸዋል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 18 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ደደቢት 10 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ ድል ቀንቶታል። ሁለት ጊዜ ብቻም አቻ ተለያይተዋል። ሁለቱ የአቻ ውጤቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመዘገቡ ናቸው።

– በርካታ ጎሎችን በሚያስተናግደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ደደቢት 32  ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 25 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

– የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀው 2009 ላይ  በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንደሚመራው ይጠበቃል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

አብዱላዚዝ ዳውድ – ኤፍሬም ጌታቸው – አንዶህ ኩዌኩ – ኄኖክ መርሹ

ፋሲካ አስፋው – ኩማ ደምሴ

ያሬድ መሀመድ – ዓለምአንተ ካሳ  – እንዳለ ከበደ

አኩዌር ቻሞ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ዋቴንጋ ኢስማ 

አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታንቢ – ተካልኝ ደጀኔ   

ሳምሶን ጥላሁን  – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን

አስራት ቱንጆ – ሎክዋ ሱሌይማን – አቡበከር ነስሩ