ለአዳዲሶቹ የሊጉ ክለቦች ጊዜ ለመስጠት ሲባል በአንድ ሳምንት ተራዝመው ነገ የሚደረጉትን ሦስት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎችን በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።
ስሑል ሽረ ከ ወላይታ ድቻ |
ስሑል ሽረዎች በታሪክ የመጀመሪያ በሆነው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸው ነገ በ09፡00 ወላይታ ድቻን ያስተናግዳሉ። ጅማ አባ ቡናን አሸንፈው ሦስተኛ ቡድን በመሆን ወደ ሊጉ የመጡት የያኔዎቹ ሽረ እንደስላሴዎች ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከትግራይ ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ ለሊጉ ጅማሮ ደርሰዋል። ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ጋር የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎችም በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ተካፋይ ነበሩ። በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ድቻዎች አምና ተዳክመው የታዩበትን ጉራማይሌ የውድድር ዓመት ዘንድሮ ላለመድገም ከሽረ ነጥብ ይዘው ለመመለስ እንደሚጥሩ ይታሰባል። ሽረዎች የመስመር ተመላላሾቻቸውን አብዝተው በማጥቃት ሂደት ላይ የሚያሳትፉ መሆኑ እና የወላይታ ድቻ የማጥቃት ጥንካሬም ከመስመር በተለይም ከቸርነት ጉግሳ የሚነሳ በመሆኑ ቡድኖቹ በሁለቱ መስመሮች የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅም እንደሚኖራቸው ይገመታል።
የስሑል ሽረው ንሰሃ ታፈሰ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆን ሸዊት ዮሃንስ ደግሞ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰው በመሆኑ ክለቡን አያገለግልም። ኃይማኖት ወርቁ ፣ እርቂሁን ተስፋዬ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ እዮብ አለማየሁ ፣ ውብሸት አለማየሁ እና ውብሸት ክፍሌ ደግሞ በወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል
ግምታዊ አሰላልፍ
ስሑል ሽረ (3-5-2)
ሰንደይ ሮትሚ
ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሃነ
ጅላሎ ሻፊ – ሰለሞን ገ/መድህን – ሄኖክ ካሳሁን – አሸናፊ እንዳለ – ሙሉጌታ ዓምዶም
ልደቱ ለማ – ኢብራሂማ ፎፋና
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
ታሪክ ጌትነት
እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ተክሉ ታፈሰ –ያሬድ ዳዊት
በረከት ወልዴ
ቸርነት ጉግሳ – ሀብታሙ ታፈሰ – ፍፁም ተፈሪ – ፀጋዬ አበራ
ሳምሶን ቆልቻ
ደቡብ ፖሊስ ከ መከላከያ |
የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን የሆኑት ደቡብ ፖሊሶች በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ነገ ከስምንት ዓመታት በኋላ የተመለሱበትን ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በ09፡00 ከመከላከያ ጋር ያደርጋሉ። ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የቡድናቸውን ክፍል በአዳዲስ ፈራሚዎች ያዋቀሩት ደቡብ ፖሊሶች አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውንም ሾመዋል። በመሆኑም በከፍተኛ ሊጉ በርካታ ግቦችን ሲያስቆጥር የምናውቀው ደቡብ ፖሊስ ከአሰልጣኙ ሹመት እና አዲስ ቡድን መሆኑን ተከትሎ ጥብቅ መከላከልን መሰረት ያደረገ አካሄድን ሊከተል እንደሚችል ይታሰባል። የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ድሎችን አጣጥመው ወደ ሊጉ የመጡት መከላከያዎች በተቃራኒው ስኬታማ የሚባሉ ዝውውሮችን በመፈፀም ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር የቀጠሉ ሲሆን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ በተመሰረተው አጨዋወታቸው እደገፉበት መናገር ይቻላል። የነገውም ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ ኳስ ለመያዝ የሚሞክር መከላከያን እና ጥንቃቄ ላይ ተመስርቶ በሁለቱ መስመሮች የመልሶ ማጥቃቶችን የሚሰነዝር ደቡብ ፖሊስን ይችላል።
የወረቀት ጉዳዮቹን ካልጨረሰው አዲሱ ፈራሚ ኤርሚያስ በላይ በስተቀር ቀሪዎቹ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች ለጫታው ብቁ ናቸው። በመከላከያ በኩል ግን ከ23 ዓመት በታች የተመረጡት ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዳዊት ማሞ የማይሰለፉ ይሆናል። ቴዎድሮስ ታፈሰ ምርጫው ውስጥ ባይካተት ኖሮም በአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ የተመለከተው ቀይ ካርድ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ያደርገው ነበር።
ዳኛ
– ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቦ የነበረው ፌደራል ዳኛ ሳህሉ ይርጋ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ደቡብ ፖሊስ (3-5-2)
ዳዊት አሰፋ
ዘሪሁን አንሼቦ – ሳምሶን ሙሉጌታ – ደስታ ጊቻሞ
ብሩክ ኤልያስ – ቢኒያም አድማሱ – ሙሉዓለም ረጋሳ – መስፍን ኪዳኔ – አዲስአለም ደበበ
በረከት ይስሀቅ – በሀይሉ ወገኔ
መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)
አቤል ማሞ
ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ
በኃይሉ ግርማ
ሳሙኤል ታዬ – ፍሬው ሰለሞን
ዳዊት እስጢፋኖስ
ተመስገን ገብረኪዳን – ምንይሉ ወንድሙ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ |
በ2010 ሲሳተፈለ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንደኛው በመውረዱ፤ ሌላኛው ደግሞ መቀመጫ ከተማውነረ በመቀየሩ የጨዋታ ጫና የቀለለት የአዲስ አበባ ስታድየም ነገ 10፡00 ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በባህርዳር ከማ መካከል ብቸኛውን የሳምንቱን ጨዋታ ያስተናግዳል። በዝግጅት ጊዜ ከሚደረጉ የክረምት ውድድሮች ራሱን አግልሎ የቆየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ዋንጫ እስከፍፃሜ ካደረገው ጉዞ በተጨማሪ የተወሰኑ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጎ ለሊጉ ጅማሮ ደርሷል። አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶን ካሰናበተ በኋላ ያለ ዋና አሰልጣኝ ነገ ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ እንደወትሮው ሁሉ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ከሚጠበቁ ክለቦች መካከል አንዱ በመሆኑ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ነጥቦች እጅግ አስፈላጊዎቹ ይሆናሉ። በአዲስ አበባ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ የደረሱት ባህር ዳር ከተማዎች ያስፈረሟቸውን አራት የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ሳያሰልፉ ነው ከፈረሰኞቹ ጋር የሚገናኙት። ሆኖም በውድድሩ ላይ በወጥነት በተጠቀሙት ቡድን በሊጉም እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት ግርማ ዲሳሳ እና ፍቃዱ ወርቁን ዋነኛ መዳረሻቸው ያደረጉ የማጥቃት ሂደቶች ነገ ከቡድኑ ይጠበቃሉ።
የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላሀዲን ባርጌቾ ፣ ሳላሀዲን ሰዒድ ፣ ታደለ መንገሻ ፣ በሀይሉ አሰፋ እና ናትናኤል ዘለቀ ከጉዳታቸው እያገገሙ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በባህርዳር በኩል ጉዳት ላይ የሚገኘው ከመከላከያ ቡድኑን የተቀላቀለው ማራኪ ወርቁ ሲሆን ዳግማዊ ሙሉጌታ ደግሞ አምና በተመለከተው ቀይ ካርድ በቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል። ከዚህ ውጪ ባህር ዳር ካለበት የተጨዋች እጥረት የተነሳ ለ23 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ያስመረጣቸው ምንተስኖት አሎ እና ወንድሜነህ ደረጄን ለዚህ ጨዋታ መልሶ ይጠቀማል። በተመሳሳይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ያቀኑት አቡበከር ሳኒ እና ፍሬዘር ካሳ ግን ነገ ክለባቸውን አያገለግሉም።
ዳኛ
– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ማኑኤ ወልደ ፃዲቅ ነው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ፓትሪክ ማታሲ
አብዱልከሪም መሀመድ – አስቻለው ግርማ – ኢሴፉ ቦውራሀና – መሀሪ መና
ሙሉዓለም ጥላሁን – ምንተስኖት አዳነ
አሌክስ ኦሮቶማ – ካሲሞ ግሎቨር – አቤል ያለው
ጌታነህ ከበደ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ምንተስኖት አሎ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – ቴዎድሮስ ሙላት
ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ
ፍቃዱ ወርቁ – ወሰኑ ዓሊ – ግርማ ዲሳሳ