ሪፖርት | የጣናው ሞገድ በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አዲስ አበባ ላያ ያለ ዋና አሰልጣኝ ባህርዳር ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተጠበቀ የ1-0 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ያደረገው ባህር ዳር ከተማም ታሪካዊ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል።

ከሰሞኑ ከዋና አሰልጣኛቸው ቫዝ ፒንቶ የተለያዩት ፈረሰኞቹ በምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመሩ ወደ ሜዳ ሲገቡ በክረምቱ ካስፈረሟቸው አዳዲስ ተጫዋቾች መካከል ስድስቱን በመጀመርያ 11 ስብስባቸው አካተው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ በአንጻሩ ያለ ውጭ ሀገር ተጫዋቾቻቸው ጨዋታውን ለማድረግ የተገደዱት ባህርዳር ከተማዎች በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የተውጣጣ ቡድንን ይዘው ለጨዋታው መቅረብ ችለዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሰሩት “ላሊበላ እና ጣናን እንታደግ” የሚል መልዕክት ባለው ማራኪ ሞዛይክ የታጀበው ጨዋታ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ባህርዳር የሜዳ አጋማሽ አድልቶ በቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ታጅቦ ቢካሄድም ምንም አይነት የግብ እድሎች ግን ሁለቱም ቡድኖች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው የመጀመሪያው ወደ ግብ የተደረገ ሙከራ የተስተናገደው በ18ኛው ደቂቃ ነበር፤ ባህርዳር ከተማዎች ወደ ቀኝ የሜዳው ጠርዝ አድልቶ ያገኙትን የቅጣት ምት ዳንኤል ኃይሉ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የፈረሰኞቹ አዲሱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በቀላሉ ይዞበታል፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር አዲስ አዳጊዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በሂደት የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በተለይም አስናቀ ሞገስና ግርማ ዲሳሳን የያዘው የቡድኑ የግራ ክፍል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ፈተና መሆን ችሏል፡፡ ግርማ ዲሳሳ በ28ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ሰብሮ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና በረኛ ያዳነበት እንዲሁም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘው ቅጣት ምት ወሰኑ አሻምቶት ኤልያስ አህመድ ሸርፎ ወደ ግብ ልኳት ኳሶ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣጭበት ኳስ የባህር ዳሮችን በጨዋታ ሂደት የበላይነት ስለመውሰዳቸው ማሳያ ይሆናል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ ተዳክሞ በተስተዋለበት የመጀመሪያው አጋማሽ ምንም አይነት የግቡ መከራ ሳያደርግ ቡድኖቹ 0-0 በሆነ ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል፡፡

በእረፍት ሰዓት በቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋቾችነትም እንዲሁም በአሰልጣኝነት ደማቅ ባለታሪክ የሆኑት የጋሽ መንግስቱ ወርቁ ልጅ የጋብቻ ስነስርአቱን ፈፅሟል ፤ በዚህም ክለቡ በማስታወሻነት አባቱ ይለብሰው የነበረውንና ማንም እንዳይለብሰው በክብር የተቀመጠው 8 ቁጥር መለያን በስጦታነት አበርክተውላቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጊዮርጊስ የተነቃቃ ቢመስልም ጎል ማስቆጠር የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች ነበሩ። በ55ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ወርቁ ከግራ መስመር ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ወሰኑ አሊ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስገኘት ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ከተወሰኑ አጋጣሚዎች ውጪ ባህርዳር ከተማዎች ወደ ኃላ በማፈግፈግ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህም ውሳኔያቸው ቡድኑን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛ አጋማሽ ለመጠቀም ምርጫው ባደረገው የቀጥተኛ አጨዋወት እጅጉን ተጋላጭ እንዲሆን አስችሏቸዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የአቻነት ጎል ፍለጋ ከመስመር እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች በሚሻገሩ ኳሶች በተደጋጋሚ የባህርዳርን ግብ ፈትሸዋል። ከነዚህም ውስጥ አሜ መሀመድ በግንባሩ ገጭቶ ሞክሯት ምንተስኖት አሎ ያዳነበት እንዲሁም ምንተስኖት አዳነ ከማእዘን የተሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ እጅግ አስቆጪ ነበሩ፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ሊሆኖባቸው የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ናትናኤል ዘለቀ እና በኃይሉ አሰፋ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

በጨዋታው የባህርዳር ከተማዎቹ ግርማ ዲሳሳ (የመስመር አጥቂ) እና ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ እጅግ ድንቅ ሆነው አምሽተዋል። የጨዋታው ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅም አራት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዘዋል።

ጨዋታው በባህርዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የጣና ሞገዶቹ የፕሪምየር ሊግ ቆይታቸው ከሜዳቸው ውጪ በተገኘ ወሳኝ ድል መክፈት ችለዋል፡፡


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK