ደቡብ ፖሊስ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስር እየተመራ እሁድ የዓመቱን የመጀመሪያ ጨዋታ አድርጎ በመከላከያ 2-1 ሽንፈትን ቢያስተናግድም አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል ራሱን ማጠናከሩን በመቀጠል ሶስት አንጋፋ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
ተከላካዩ አበባው ቡጣቆ፣ ጋናዊው ተከላካይ አዳሙ መሀመድ እና መከላከያን በገጠሙበት ጨዋታ የቀድሞው ክለቡን ገጥሞ ግብ ያስቆጠረው አጥቂው የተሻ ግዛው ናቸው በአንድ ዓመት ውል ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀሉት።
ከ1990ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም ጊዜያትን ያሳለፈው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግራ መስመር ተከላካይ አበባው ቡጣቆ በተለይ ከቅጣት ምት በሚያስቆጥራቸው ኳሶቹ የሚታወቅ ሲሆን በ2006 ወደ ሱዳን አምርቶም ለአንድ የውድድር ዓመት ተጫውቶ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መመለሱ ይታወሳል። ተጫዋቹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኃላ ወደ ጅማ አባጅፋር ሊያመራ ነው ሲባል ቢቆይም ደቡብ ፖሊስን ማረፊያውን አድርጓል፡፡
ሌላኛው ፈራሚ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ አዳሙ መሐመድ ነው። የውጭ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የፈረመው ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ2003 ሲሆን በሊጉ ረጅም ዓመት የቆየ የውጪ ዜጋ ተጫዋች ነው። የቀድሞው የደደቢት ተጫዋች በ2008 ወደ ወልዲያ ካመራ በኋላ የመጀመርያዎቹን ሁለት ዓመታት ደንቅ ጊዜ ቢያሳልፍም አምና በጉዳት ለረጅም ወራት ከሜዳ ርቆ እንደነበር የሚታወስ ነው። ወደ ሀገሩ ጋና አምርቶ ለህክምና ከቆየ በኃላ አገግሞ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው አዳሙ በምክትል አሰልጣኝነት በደደቢት አብሮት ከሰራው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር ዳግም ተገናኝቷል።
አጥቂው የተሻ ግዛው ሌላኛው ፈራሚ ነው። ትላንት ደቡብ ፖሊስ በመከላከያ በተሸነፈበት ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ በመጫወት ግብም አስቆጥሯል። በኒያላ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ዳሽን ቢራ መጫወት የቻለው አጥቂው ወደ ከፍተኛ ሊጉ አዲስ አበባ ከተማ እንዳመራ ቢነገርም በአንድ ዓመት ውል ደቡብ ፖሊስን ተቀላቅሏል።