የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-1 ሀዋሳ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በአጼዎቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኞቹ የሰጡትን አስተያየት እነሆ!

” ተጫዋቾቼ ላይ ከቀን ወደ ቀን መሻሻል እያየሁ ነው።” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ዳኛው ውሳኔ

ሙሉ በሙሉ ዳኛውን መገምገም አልፈልግም። ጎል መሆኑን አፅድቆ ሁላችንም እየጨፈርን ባለበት ሰዓት ነው ያ ሁሉ ትርምስ የተፈጠረው። ቀደም ብሎ ግብ አይደለም ወይም ጥፋት ተሰርቶበታል ቢል አኛ ነበርን ተጠቃሚዎች። ጥፋት ተሰርቷል ቢል እንኳን ፌሽካ ነፍቻለሁ ካለ ፍጹም ቅጣት ምት እዛው ላይ በመስጠት ጨዋታውን መቆጣጠር ይችል ነበር። ነገር ግን እንደሰው ሊሳሳት ይችላል መቀበል ነው። እናም ያ አጋጣሚ ጨዋታውን ቀይሮታል ።

ስለ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ 

እውነት ለመናገር ሁሉም ተጨዋቾች በጣም ጥሩ ነበሩ። ከቀን ወደ ቀን የተሻሻሉ ነገሮች ሁሉም ላይ አይቻለሁ። ሱራፌል ግብ አስቆጥሯል፤ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጭም የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል። እንደ አጠቃላይ ሁሉም ጥሩ ነበሩ።

ስለቀጣይ ጨዋታ

መቐለ ጠንካራ ስብስብ ያለው ቡድን ነው። ሁለቱንም ጨዋታ ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱም በሜዳው ነበር፤ እንደ አጋጣሚ ሶስተኛውም በሜዳው ነው የሚያደርገው። ለነሱ ጥሩ ነው። እኛ ደግሞ ጥንቃቄ አድርገን በሽንፈት ሆነ በማሸነፍ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን አይተን በማስተካከል ከነሱ ጋር ያለውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንሰራለን ።


” የተፈጠረው ነገር ደስ አይልም” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ዳኛው ውሳኔ 

ሁለተኛው ግብ ሲቆጠር ዳኛው ፊሽካ ነፍቷል። በዛ ምክንያት የኛ ተጫዋቾች ቆመዋል። በዛ ምክንያት ግቡ ተቆጠረ ግብ ነው ብሎ አፀደቀ፤ ሄደን ስናናግረው ፊሽካ መንፋቱን አመነ። የኛን አንድ ተጫዋቾች አስወጥቶ ግቡን ሻረው። ከዛ እንደገና ፍጹም ቅጣትምት ሰጠ። ቢሆንም ከ ሳጥን ውጭ ስለነበር ፍጹም ቅጣት ምት አያሰጥም ነበር። በዚህ ሁኔታ ሁለተኛ ግብ ተቆጠሮብናል። የተፈጠረው ነገር ደስ አይልም።

የአዳነ ግርማ ቀይ ካርድ እና የውሳኔው ተፅዕኖ

በምን እንደሆነ አናውቅም፤ ለምን እንደተሰጠውም አናውቅም። ምን አልባት አሁን አዳነን በቀይ ሲያስወጣው ጥፋቱን ሰርቷል ብሎ ከሆነ ጥፋቱ የተሰራው ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጭ ነው። ግቡን ሲሽረው አዳነን አስወጣው። የግቡ መሻር ምክንያት አዳነ ይመስለኛል። ያ ቅጣት ምት ከሳጥን ውጭ ነበር መመታት የነበረበት። ካልሆነ ግን አዳነን ማስወጣት አልነበረበትም። የተምታታ ነገር ነው የተከሰተው። እንደ አጠቃላይ የዳኛው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተፅዕኖ ነበረው። ተጫዋች በቀይ ወጥቶብናል። ያለ አግባባ ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል። ምንም ጥርጣሬ የለውም ሙሉ ለሙሉ ተፅዕኖ አድርሶብናል።