በስድስት ቡድኖች መካከል ለአምስት ቀናት የታካሄደው መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ፌስቲቫል ቅዳሜ ፍፃሜውን አግኝቷል።
እግር ኳስን የሚሰሙ ብቻ ሳይሆን መስማት የተሳናቸውም መጫወት እንደሚችሉ የተቀረው ዓለም እንደሚያደርገው ኢትዮጵያም ይህን ማድረግ እንዳለባት በሚል ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ ከጥቅምት 20 – 25 መስማት በተሳናቸው ከስድስት ክልሎች በመጡ የእግር ኳስ ቡድኖች መካካል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ፌስቲቫል ፍፃሜውን አግኝቷል።
ቅዳሜ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ለፍፃሜ በደረሱት ሀዋሳ እና ሆሳዕና መካከል በተካሄደው ጨዋታ ሀዋሳዎች ከፍፁም የበላይነት ጋር 4 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። ከሀዋሳ የድል ጎሎች መካከል የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ያጠናቀቀው ትንሣኤ አበበ ሐት-ትሪክ በመስራት ሦስት ሲያስቆጥር ቀሪዋን አንድ ጎል ጌታቸው ጌታሁን አክሎ የፌስቲቫሉ ቻምፒዮን መሆን ችለዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፌስቲቫሉ አሸናፊ ለሆኑት ሀዋሳዎች በዕለቱ የክብር እንግዳ አማካኝነት የዋንጫ ሽልማት ተበትክቶላቸዋል። ለመጀመርያ ጊዜ እንደተዘጋጀ በተነገረለት በዚህ ፌስቲቫል መስማት የተሳናቸውን እግር ኳስ ተጫዋቾችን ከእያሉበት ክልል አሰባስቦ በአንድ ቦታ ውድድር ማዘጋጀቱ እንደ መልካም ጅማሮ የሚወሰድ ነው። ነገር ግን በቀጣይ እነዚህን መሰል ውድድሮች ሲዘጋጁ ከመርሀግብር አወጣጥ እና ሌሎች ችግሮችን ጋር ተያይዞ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮችን በማረም ፌስቲቫሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልክታችን ነው።