መከላከያ – የ2007 የኢትዮጵያ ዋንጫ ቻምፒዮን

መከላከያ የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ ቻምፒዮን ሆኗል፡፡ ዛሬ 10 ሰአት ላይ በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ መከላከያ ሀዋሳ ከነማ በቀላሉ 2-0 በመርታት የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

መከላከያ ከግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ሽመልስ ተገኝ ወደ ቋሚ አሰላለፉ የተመለሰ ሲሆን በሀዋሳ ከነማ በኩል ደግሞ ደስታ ዮሃንስ ተስፋ ኤልያስን ፣ አንተነህ ተሸገር ኤፍሬም ዘካርያስን ተክተው በቋሚ አሰላለፉ ተካተዋል፡፡

የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ እምብዛም የተመልካች ተርኩረትን የማይስብ የነበረ ሲሆን ሀዋሳ ከነማዎች አመዛኙን ክፍለ ጊዜ በመሃል ሜዳ የተገደበ የኳስ ቁጥጥር ነበራቸው፡፡ በአንፃሩ መከላከያዎች ኳስ በእግራቸው ስትገባ በፍጥነት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመድረስ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ18ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከመስመር የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ ቢገጨውም የግቡን ቋሚ ገጭታ ወጥታለች፡፡ ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ነጂብ ሳኒ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ዮሃንስ በዛብህ ይዞበታል፡፡

በ31ኛው ደቂቃ የጨዋታው ኮከብ የሚያሰኘውን ድንቅ ብቃት ሲያሳይ የዋለው ፍሬው ሰለሞን ለምንይሉ ወንድሙ ያሻገረውን ግሩም ኳስ ምንይሉ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመቀየር መከላከያን መሪ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በመከላከያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በ2ኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ሀዋሳ ከነማን የተቀላቀለው አስቻለው ግርማ አንተነህ ተሸገርን ቀይሮ በመግባት ለክለቡ የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል፡፡

በ51ኛው ደቂቃ የመጀመርያዋን ግብ ያቀበለው ፍሬው ሰለሞን ግብ በማስቆጠር መከላከያ ወደ ዋንጫው ይበልጥ እንዲጠጋ አድርጓል፡፡ ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ምንይሉ ወንድሙ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ለመከላከያ 3ኛውን ግብ የማስቆጠር አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ሀዋሳ ከነማ ከግቦቹ መቆጠር በኋላ የተሸለ የግብ እድል ለመፍጠር የተንቀሳቀሰ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ፣ በ81ኛው ደቂቃ በረከት ይስሃቅ ወደ ግብ የሞከሯቸውን ኳሶች ይድነቃቸው ኪዳኔ አድኗቸዋል፡፡ ጨዋታውም በመከላከያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የመከለካያ አምበል የሆነው ሚካኤል ደስታ ከእለቱ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡

IMG_1795

ያጋሩ