የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኮከቦች ሽልማት ጉዳይ ግራ አጋቢ ሆኗል

በ2010 ፌዴሬሽኑ ያወዳደራቸው ሰባት ሊጎች ኮከቦችን ሽልማት ኅዳር መጀመርያ ላይ ይደረጋል ቢባልም ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።

ለሁለተኛ ጊዜ በሚዘጋጀው በዚህ የኮከቦች ሽልማት ከአምናው ልምድ በመውሰድ ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ ይደረጋል ቢባልም እስካሁን ሳይደረግ መቆየቱ እንዳለ ሆኖ በአንዳንድ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ዘንድ ቢቀር የሚል ሀሳብ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም “ከአምናው የተሻለ መርሀግብር ማድረግ ባይቻል እንኳ ከሚቀር ይደረግ” በሚል ኅዳር 6 ለማድግ ተወስኗል። ሆኖም ቀኑ ይታወቅ እንጂ ሽልማቱ የሚዘጋጅበት ቦታ እና ሰዓት እስካሁን አለመታወቁን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ እና የሁሉንም የኮከቦች የሽልማት ስነ ስርአት በአንድ ሆቴል ለማድረግ እንዲሁም የተሸላሚዎችን የሽልማት ክፍያን መጠን ከፍ ለማድረግ በማሰብ ከናታኔም አድቨርታዚንግ ጋር በመተባበር ለመጀመርያ ጊዜ የ2009 የውድድር ዓመት የስድስቱ ሊጎች (ፕሪምየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ፣ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ፣ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ እና ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ) ኮከብ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች ፣ ጎል አስቆጣሪዎች እና የምስጉን ዳኞች ሽልማት መርሐ ግብርን ጥቅምት 19 ቀን 2010 ላይ በካፒታል ሆቴል በድምቀት ማካሄዱ ይታወሳል። 

ዘንድሮ መከናወኑ አጠራጣሪ የሆነው የኮከቦች ሽልማት ከተካሄደ ከላይ ከተጠቀሱት ሊጎች በተጨማሪ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ሽልማት የሚከናወን ሲሆን መርሐ ግብሩ እንደተገመተው ሳይከናወን ከቀረ ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከተከሰቱ መጥፎ ክስተቶች መካከል ተመዝግቦ የማለፍ እጣ ይኖረዋል።