ከቀናት በፊት የአፍሪካ ቻምፒዮስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ እንደማይመራ ተገልፆ የነበረው ባምላክ ተሰማ በካፍ ድንገተኛ ጥሪ ሁለተኛውን የፍፃሜ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራል፡፡
በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የፊታችን ዓርብ ምሽት በቱኒዚያ ኤስፒሪያንስ ደ ቱኒዝ ከአልሀሊ በሚያደርጉት ሁለተኛ የፍፃሜ ጨዋታ የ2018/19 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜውን ያገኛል። በመጀመሪያው የፍፃሜ ጨዋታ ግብፅ ላይ ባለሜዳው አልሀሊ በአወዛጋቢ ዳኝነት በታጀበው ጨዋታ 3-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል። በካይሮው ቦርግ አል አረብ ስታድየም የተደረገውን ያን ጨዋታ አልጄሪያውያኑ መሕዲ ቻሬፍ (ዋና) እና አብድልሀክ ኢትቻል (ረዳት) እንዲሁም ቡሩንዲያዊው ጃን ክላውድ ቢሩሙሻሁ ነበሩ የመሩት። በአወዛጋቢ ውሳኔዎች የተሞላው እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠበት ጨዋታም የአልሀሊው ኦሌድ አዛሮ የዳኛን ውሳኔ በማሳሳት ሁለት ጨዋታዎችን እንዲቀጣም ያደረገ ነበር።
ሁለተኛው እና የመጨረሻውን አሸናፊ የሚለየው ጨዋታ ደግሞ የፊታችን ዓርብ ምሽት ቱኒዝ ላይ ይደረጋል። ይህን ጨዋታ አስቀድሞ ጋምቢያዊው ዋና ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ ይመራዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያዊው በዓምላክ ተሰማ እንዲመራው ካፍ ትላንት ለዳኛው በላከለት መልዕክት መግለፁን ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ተናግሯል ፡፡ ከቀናት በፊት ወደ ግብፅ አምርቶ በፍፃሜ ጨዋታዎቹ በአዲስ መልክ ተግባራዊ በሆነው የVar ቴክኖሎጂ ዙሪያ ስልጠና ወስዶ የተመለሰው በዓምላክ የካፍ የዳኞች ኮሚቴ በተሻለ ብቃት ጨዋታውን ይመራዋል በማለት ዕምነቱን ጥሎበታል።
በአፍሪካ መድረክ የተለያዩ ውድድሮችን በመምራት በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት የአህጉሪቱ ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያውን የፍፃሜ ጨዋታ ከዳኘ በኃላ አሁን ደግሞ ሁለተኛውንና ወሳኙን ጨዋታ የሚመራ ይሆናል። በዓምላክ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየትም “ያልጠበኩት ነው ፤ እንደማላጫውት ነበር የተነገረኝ አሁን ግን እንደማጫውት ሲነገረኝ በጣም ደስተኛ ሆኛለው። በሚገባ እንደምወጣውም ዕምነት አለኝ” ብሏል። አርቢትሩ ዛሬ በኤምባሲ የቪዛ ጉዳዩችን ካጠናቀቀ በኃላ ነገ ወደ ቱኒዚያ ረፋድ እንደሚያመራ ይጠበቃል፡፡