አርብ ሊከናወኑ መርሐ ግብር ወጥቶላቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዓመት ሁለተኛ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች በብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።
አርብ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ሊደረጉ ከነበሩ ሶስት ጨዋታዎች መካከል ሐረር ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ለዋልያዎቹ እና ለ23 ዓመት በታች ቡድን አምስት ተጫዋቾች (ሳምሶን አሰፋ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ፍቃዱ ደነቀ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ እና ገናናው ረጋሳ) በማስመረጡ ሲራዘም የወላይታ ድቻ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታም በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና አራት ተጫዋቾች (አዲስ ግደይ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ) በማስመረጡ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ታውቋል። ሌላኛው በባህር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ መካከል የሚደረገው ጨዋታም ወደ ሌላ ጊዜ የመተላለፍ እጣ የደረሰው ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ጨዋታውን በሰላም እንዲከናወን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ቢገልፅም ፌዴሬሽኑ ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የማራዘም ውሳኔ ላይ እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል።