በደጋፊዎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስቀረት የታሰበ ዕርቀ ሰላም በአዳማ አበበ ቢቃላ ስታድየም ዛሬ ረፋድ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ተካሄደ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታድየምም ሆነ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ጨዋታዎች በተደረጉ ቁጥር ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ በደጋፊዎች መካከል በሚፈጠር መቃቃር አላስፈላጊ ግጭቶች ሲስተዋሉ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህን አለመግባበት ለማስቀረት በማሰብም ዛሬ ረፋድ ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሐ (ኢንጂነር) የወጣቶች ስፖርት ሚኒስትር ተወካይ ፣ የአዳማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ፕሬዝደንት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አስኪያጅ እንዲሁም በርከት ያሉ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች በታደሙበት የዕርቀ ሰላም ጉባኤው ተካሂዷል። በአባገዳዎች የፀሎት ፣ የምርቃት እና የዕርቅ ሥነ ስርዓት በጀመረው በዚህ መድረክ በሁለቱ ክለቦች መካከል ቀድሞ የነበረው መልካም እና የጠነከረ ግንኙነት ጥቃቅን በሚባሉ ችግሮች መነሻነት በተፈጠሩ አለመግባባቶች ቢደፈርስም ችግሩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ ሰላም የሰፈነበት እንዲሁም ለሌሎች ክለቦች ዓርዓያ እንዲሆን በሚል ዕርቁ ተካሂዷል።
በቀጣይ ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ውይይትም ተደርጓል። በዚህም በዕለቱ የተገኙት እንግዶች በተፈጠረው ዕርቀ ሰላም ደስተኛ በመሆን በቀጣይ ለስፖርታዊ ጨዋነት ሁላችንም የበኩላችንን እስተዋፆኦ እናድርግ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመጨረሻም የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በመዘመር በአስደናቂ ወንድማዊ ፍቅር የዕርቀ ሰላሙ መድረክ ፍፃሜውን አግኝቷል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን በመቐለ 70 አድርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንዲሁም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመቅረፍ እንደነዚህ ያሉ መሰል መድረኮችን በቀጣይ እነደሚያዘጋጁ ለማወቅ ችለናል።