አስተያየት | በዘርዓይ ኢያሱ |
ባለፈው እሁድ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን ታሪካዊ ድል ሲያቀዳጀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ጨዋታዎችን እንዴት ሊሄድበት እንደሚገባ ጥቆማ ያገኙበት ጨዋታ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ በዚህ ጨዋታ ውስጥ በርካታ ሊነሱ የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በእለቱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንጋታ የመረጠውን የጨዋታ ሲስተም መነሻ በማድረግ የታዩ ጉድለቶች ላይ ለማተኮር መርጫለሁ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለተጠበቀ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ መነሻ ፎርሜሽኑ 4-4-2 ዳይመንድ ነው፡፡ ይህ ፎርሜሽን መደበኛ ከሚባለው 4-4-2 የቅርፅና የተጫዋቾች ስምሪት ልዩነት አለው፡፡ ታዲያ በሃገራችን ይህንን የጨዋታ ሲስተም የሚደፍሩ በጣም ጥቂት አሰልጣኞች ሲሆኑ አንዱ የመከላከያው ሥዩም ከበደ ነው፡፡ ስዩም ከበደ አዲስ አበባ ከተማን በያዘ ግዜ ይህን አጨዋወት ደጋግሞ ሲጫወት አውቃለሁ፡፡ በተረፈ ግን ብዙዎቹ ይህንን ለማድረግ ድፍረቱ የሌላቸው ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ተጨዋቾቹ በቀላሉ ለመረዳት ስለሚቸገሩ ነው፡፡
ይህንን ግን ዘሪሁን ሸንገታ ሰሞኑን ሞክሮ አሳይቶናል፡፡ አሰልጣኙ ይህንን ማድረጉ ስህተት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጨዋታ በአማካይ ስፍራ ይጫወቱ ዘንድ የመረጣቸው ተጨዋቾች ለቦታው ብቁ ስላልነበሩ ዋጋ አስከፍሎታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ተጨዋቾች ከእንዲህ አይነቱ አጨዋወት ጋር ራሳቸውን ያላላመዱ በመሆኑ ሲስተሙን ወይም የጨዋታ ዘይቤውን ለመተግበር ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት የዳይመንድን ጣህሙን ለመቃደስ ሳኝችል ቀርተናል፡፡ 4-4-2 ዳይመንድ በጣም ጥልው ግንዛቤንና ጨዋታ ማንበብን የሚጠይቅ ፎርሜሽን በመሆኑ ለዚህ አጨዋወት የሚሆኑ ተጨዋቾችን መመልመል ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
4-4-2 ዳይመንድ
ይህ ፎርሜሽን ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት አመቺ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግራና በቀኝ በኩል ያሉት አማካዮች ጋዲሳ መብራቴና አሜ መሃመድ ወደ ውስጥ አጥብበው ሲጫወቱ የመስመር ተከላካዮቹ አብዱል ከሪም መሃመድና ሄኖክ አዱኛ የሜዳውን መስመር ይዘው ለማጥቃት እንዲሄዱ ይጋብዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱን አጥቂዎች (ጌታነህ ከበደንና አሌክስ አርቶማ) እንዲሁም 10 ቁጥር ቦታ ላይ የሚጫወተውን ካሲም ታይሰንን ጨምሮ አምስት ተጨዋቾች ማጥቃት ላይ እንዲሳተፉ ያርጋቸዋል፡፡ ይህ ማለት ሙሉዓለም መስፍንን፤ አሜ መሃመድንና ጋዲሳ መብራቴን ሳይጨመር ሲሆን አሜ መሃመድና ጋዲሳ መብራቴ ከተጨመሩበት ደግሞ ሰባት ተጨዋች በማጥቃት ውስጥ እንዲሳተፉ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የማጥቃት አማራጩን አብዝቶ የሚጫወተውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጠብቀን ነበር፡፡
በተለይ ፎርሜሽኑ የመስመር አጥቂዎችን የማያሰማራ በመሆኑ የሄኖክ አዱኛና የአብዱልከሪም መሃመድ በመስመር በኩል ለማጥቃት በጥልቀት መሄድ ሜዳውን ከማስፋትና ለጌታነህ ከበደና ለ19 ቁጥሩ አሌክስ አርቶማ ነፃ ቦታዎችን ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ አማካዮች ጋዲሳ መብራና አሜ መሃመድ ከፎርሜሽኑ ጋር የሚጣጣም የቴክኒክ ብቃት ስላልነበራቸው የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ሚና ውስንነት ነበረው፡፡
ጋዲሳና አሜ መሐመድ
ሁለቱ ተጨዋቾች ማለትም ጋዲሳ መብራቴ እና አሜ መሃመድ ስምሪት ከሙሉዓለም መስፍን ግራና ቀኝ በኩል ሆኖ 12 ቁጥሩ ካሲም ታይሰን ደግሞ በትይዩ ሆነው ነበር የተጫወቱት፡፡ በዚህ የጨዋታ ቅርፅ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኳስ በሚይዝበት ግዜ ጋዲሳና አሜ ወደ ውስጥ በማጥበብ ሲጫወቱ የመስመር ተከላካዮቹ የሜዳውን ጥግ ይዘው በጥልቀት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመግባት የመስመር አጥቂዎችን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ይቻላል፡፡
እንዲሁም በመከላከል ግዜ ጋዲሳና አሜ ወደ መስመር ይወጡና በሁለቱም በኩል ያሉትን የመስመር ተከላካዮችና የመስመር አጥቂዎችን የሚያገናኘውን መስመር በመዝጋት የተጋጣመያቸውን የማጥቃት ሃይል ማዳከም ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱ አማካዮች ኳስ በሄደችበት አብረው በመክነፋቸው በማጥቃትና በመካላከል ግዜ የነበራቸው ሽግግር ሚዛኑን ባለመጠበቁ የሄኖክና የአብዱልከሪም የማጥቃት ሚና ውስንነት ገጥሞታል፡፡
ካሲሙ ታይሰን
ካሲሙ ታይሰን ከጌታነህ ከበደና ከአሌክስ አርቶማ ጀርባ በመሆን የአስር ቁጥር ሚና ለመወጣት ሲሞክር ተመልክተናል፡፡ የተጨዋቹ ሚና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ ማድረስ ይህን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ከሌለ ደግሞ ለማጥቃት በጥልቀት የሚሄዱት የመስመር ተከላከዮቹ ካሉ ወደ መስመር ማውጣጥ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ለካሲም ታይሰን አስቸጋሪ ስለነበር ተጨዋቹ ከቡድን ስራ ይልቅ ግላዊ ነገሩ በዝቶ ታይቷል፡፡ ይህ ማለት ግን ተጨዋቹ ሙሉ ለሙሉ ችግር ነበረበት ማለት አይደለም፡፡ በመከላከል ግዜ ያሳየው እንቅስቃሴ ስለ ቦታው ጥቂት ግንዛቤ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ ባህር ዳር ከተማ ኳስ ከራሱ ሜዳ በቅብብሎሽ ለመውጣት በሚያደርገው እንስቃሴ ካሲም ታይሰን የባህር ዳር ከተማው አማካይ ፍቅረሚካኤል አለሙ ኳስ ተቀብሎ እንዳያሰራጭ ለማድረግ ጫና ሲፈጥረብት ቆይቷል፡፡
ተጨዋቹ የቡድኑን ጨዋታ የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ ከታክቲክ አንፃር ካየነው በዚህ ረገድ ታይሰን ጥሩ ሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡
አሌክስ አሮቶማል
ተክለ ሰውነቱ ገዘፍ ብሎ የሚታየው አሌክስ አርቶማል ከጌታነህ ከበደ ጋር ተጣምሮ ብንመለከትም ሜዳ ውስጥ በነበረው ቆይታ የተሳካ ግዜ አላሰለፈም፡፡ ግዙፍነቱ ከረጅም ቁመቱ ጋር ተደምሮ የአየር ላይ ኳሶች አጠቃቀምና ሸፍኖ በመጫወት በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስን ከፊት ይረዳዋል የሚል እምነት የብዙዎቻን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የባህር ዳር ከተማ ተከላካዮች በቀላሉ ተቆጣጥረውታል፡፡
ምናልባት ከዚህ በኋላ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች መሻሻሎችን ያሳይ እንደሆነ እንጂ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያሳየው አቋም ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጨምርለት አዲስ ነግር እንደማይኖር መናገር ይቻላል፡፡ ግን ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረጃጅም ኳሶችን መጫወት በሚፈልግ ግዜ ሊጠቅም እንደሚችል መገመት ይኖርብናል፡፡
በኃይሉ ለምን ቀድሞ አልገባም?
በሁለተኛው ግማሽ በሃይሉ አሰፋ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጭኖ ከመጫወቱ ባሻገር ከመጀመሪያ ግማሽ በተሻለ የጎል እድሎችን ፈጥሯል፡፡ ታዲያ የዚህ ተጨዋች መጫወት የዚህን ያህል ተፅኖ መፍጠር ከቻለ ለምን ቀድሞ አልገባም የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እንደ እኔ አረዳድ በሃይሉን ከቋሚ አሰለላፍ ውጪ ደረገው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የመረጠው 4-4-2 ዳይመንድ ፎርሜሽን ነው፡፡ለምን ቢባል ይህ ፎርሜሽን እንደ በሃይሉ አሰፋና አቡበከር ሳኒ ያሉ የመስመር አጥቂዎችን አይፈልግም፡፡ በሃይሉ ከጉዳት ነው የተመለሰው፡፡ ስለዚህ የአካል ብቃቱ 90 ደቂቃ ላያጫውተው ይችላል፡፡ አቡበከር ሳኒ ደግሞ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት ዝግጅት ላይ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህ ሁለት ተጨዋች በሌሉበት የመስመር አጥቂዎችን የሚፈለገውን ፎርሜሽን መጠቀም ለአሰልጣኝ ዘርሁን ሸንገታ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባትም በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል አሰልጣኙ ሌላ አማራጭ ሊወስድ የቻለው፡፡
ማጠቃለያ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በአንደኛ ደረጃ በሚመርጠው የጨዋታ እቅዱ ተጫውቷል ለማለት አልደፍርም፡፡ ምክንያቱም በ2010 የውድድር ዓመት በቋሚ አሰላለፍ ሲጠቀሙባቸው የነበሩት ተጨዋቾች በተለያዩ ምክንያቶች በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አልነበሩም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አዲስ ፈራሚዎቹ ሁለት የውጭ ሃገር ተጨዋቾችም አልተጫወቱም፡፡ ለዚህም ነው በአንደኛ ደረጃ በሚመርጠው የጨዋታ እቅዱ አልተጫወተም ለማለት የወደድኩት፡፡
*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡
*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com
ሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ ላይ አስተያየት መጻፍ ይፈልጋሉ? |
ሶከር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያላችሁን አስተያየት አዘል ተቀብላ በድረ-ገጿ ላይ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ትገልጻለች፡፡ |
የምንቀበላቸው ጽሁፎች
-በኢትዮጵያ እግርኳስ እና ተያያዥነት ያላቸው ማናቸውንም ርዕሰ-ጉዳዮች -ከ800 ቃላት ያላነሰ ወይም በላይ የሆነ -በሌላ አካል ወይም ግለሰብ ከዚህ በፊት ተጽፎ ያልቀረበ -ስነ-ጽሁፋዊ ይዘቱ ከፍ ያለ እና ለአንባቢያን ግልጽ የሆነ -በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የተጻፈ – ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል -የግለሰብ ወይም ቡድን እምነት፣ ዘር፣ ሀሳብ እና አመለካከት፣ ሰብዓዊ ክብር የማያንቋሽሹ |
አስተያየትዎን በፋይል አያይዘው (Attach አድርገው) በዚህ ኢሜይል አድራሻ ይላኩልን:- abgmariam21@gmail.com |