ካሜሩን 2019| ወቅታዊ መረጃዎች በጋና ብሔራዊ ቡድን ዙርያ

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ ወሳኝ የማጣርያ ጨዋታዎች በኅዳር ወር ይከናወናሉ። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋናም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ጋር ትጫወታለች። 

በመጀመርያ የምድብ ስድስት ጨዋታዋ ኢትዮጵያን ባባ ያራ ስታድየም ላይ 5-0 አሸንፋ በያዘችው ሶስት ነጥብ ኬንያን እየተከተለች የምትገኘው ጋና ያለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተጋጣሚዋ ሴራሊዮን በፊፋ በመታገዷ ምክንያት ሳትጫወት ቀርታለች። 

20 ተጫዋቾች ተጠርተዋል

ግብ ጠባቂዎች (2)

ሪቻርድ ኦፎሪ (ማርቲዝበርግ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ላውረንስ አቲ (ሶሾ/ፈረንሳይ)

ተከላካዮች (6)

ሐሪሰን አፉል (ኮሉምበስ ክሪው/አሜሪካ)፣ ጆን ቦዬ (ሜትዝ/ፈረንሳይ)፣ ለሞር አግቤንዬኑ (ስፖርቲንግ ሊዝበን/ፖርቱጋል)፣ አንዲ ይአዶም (ሬዲንግ/እንግሊዝ)፣ ጆናታን ሜንሳህ ( ኮሉምበስ ክሪው/አሜሪካ)፣ ካሲም አደምስ (ሆፈንሄይም/ጀርመን)

አማካዮች (8)

አንድሬ አዬው (ፌነርባቼ/ቱርክ)፣ ሙባረክ ዋካሶ (አላቬስ/ስፔን)፣ ኩዋዶ አሳሞአህ (ኢንተር ሚላን/ጣልያን)፣ አፍሪዬ አኳህ (ኢምፖሊ/ጣልያን)፣ ክሪስቲያን አትሱ (ኒውካስል/እንግሊዝ)፣ ናና አፖማህ (ዋስላንድ በቨረን/ቤልጂየም)፣ ቶማስ ፓርቴይ (አትሌቲኮ ማድሪድ/ስፔን)፣ ማጂድ አሽሜሩ (ሴይንት ጋለን/ስዊዘርላንድ)

አጥቂዎች (4)

አሳሞአህ ጊያን (ካይዘሪስፖር/ተለርክ)፣ ጆርዳን አዬው (ክሪስታል ፓላስ/እንግሊዝ)፣ ማጂድ ዋሪስ (ኖንት/ፈረንሳይ)፣ ኢሚኑኤል ቦአቴንግ (ሌቫንቴ/ስፔን)


ከአዲስ አበባ በፊት ኬንያ …

ጥቋቁር ከዋክብቶቹ ሰኞ ኬንያ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ከናይሮቢ 76 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ናይቫሻ ሪዞርት የሚከትሙ ሲሆን እስከ ጨዋታው መዳረሻ ድረስ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሏል። ” ወደ ኬንያ መጓዝ የመረጥነው ከአዲስ አበባ ጋር የሚቀራረብ ከፍታ ፈልገን ነው። ለተጫዋቾቻችን ጠቃሚ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።” ሲሉ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ክዌሲ አፒያ ወደ ኬንያ የሚጓዙበትን ምክንያት ገልጸዋል።

ክዌሲ አፒያ ከአዲስ አበባ በድል መመለስን አልመዋል

የጋና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክዌሲ አፒያ ስለ ቡድናቸው ወቅታዊ ሁኔታ ለጋናው ዴይሊ ግራፊክስ በሰጡት አስያየት ትኩረታቸው ኢትዮጵያን አሸንፎ መመለስ እንደሆነ ገልጸዋል።

” ተጫዋቻችን ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ ተከታትለናል። ስለዚህ ትኩረታችን ኢትዮጵያን አሸንፈን ወደ አፍሪካ ዋንጫው በማለፍ ላይ ነው። ሁለት ጨዋታዎች ይቀሩናል። ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረንን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርብናል፤ ከዛ በኋላ የመጨረሻውን ጨዋታ ዘና ብለን ማድረግ እንችላለን። “

” እስካሁን በቡድኔ ውስጥ የጉዳት ስጋት የለም። በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የሚያሳዩትን አቋም ተመልክቼ ለኢትዮጵያው ጨዋታ የሚሆነኝን የመጨረሻ ቡድን የምመርጥ ይሆናል።”