በግብፅ ሊግ የሚጫወቱት የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ዑመድ ኡኩሪ (ስሞሀ) እና ጋቶች ፓኖም (ኤል ጎዋና) በግብፅ ሊግ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት 03:00 እርስ በእርስ ይገናኛሉ።
ከመከላከያ የተገኘውና በ2004 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቶ ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ዑመድ በ2007 የሳላዲን ሰዒድ እና ሽመልስ በቀለን መንገድ በመከተል ወደ ግብፁ ክለብ ኢቲሃድ አሌሳንድሪያ በማምራት ነበር የውጪ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው። በኢቲሃድ ብዙም ሳይጫወት እና ሳይስማማ ቀርቶ ተመልሶ ወደ ሀገሩ ከመጣ በኋላ ዳግም ወደ ግብፅ በማምራት ለኤንፒ ፊርማውን ቢያኖርም በተመሳሳይ ብዙ ሳይጫወት ቆይቶ ወደ ሦስተኛ ክለቡ እና የተሳካ ቆይታ ወዳደረገበት ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ አምርቶ በ11 ጎሎች በማስቆጠር በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጎሎችን ያስቆጠረ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ በመሆን አጠናቋል። (ምንም እንኳ ከወዲሁ 7 ጎሎች ላይ የደረሰው ዓመት ሽመልስ በቀለ ዘንድሮ ካልሰበረበት በቀር።) ባለፈው ዓመት ወደ ስሞሀ ያመራው ዑመድ የውድድር ዓመቱ ፍፃሜ ገና ቢሆንም ከአምናው አቋሙ አንፃር ዘንድሮ እስካሁን ለክለቡ ምንም ጎል ሳያስቆጥር የተቀዛቀዘ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
ከኢትዮጵያ ቡና የተገኘው ጋቶች ፓኖም በበኩሉ በውጭ ሀገር የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ባለፈው ዓመት ወደ ሩሲያ በማቅናት ከሙከራ በኋላ ነበር ለአንዚ ማካቻካላ ፊርማውን ያኖረው። ሆኖም በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ከመጫወት በቀር ብዙም የመጫወት እድል አለማግኘቱን ተከትሎ በስምምነት በመለያየት ወደ ሀገሩ ተመልሷል። በኋላም ወደ ደቡብ አፍሪካው ቤድቬስት ዊትስ ለሙከራ ቢያቀናም ሳይሳካ ለመቐለ 70 እንደርታ ስድስት ወራት ያህል ቆይታ አድርጎ በዘንድሮ ዓመት ወደ ግብፁ ክለብ ኤል ጎውና በመሄድ በአመዛኙ የክለቡ ጨዋታዎች ላይ የቋሚ ተሰላፊነት እድል ማግኘት ችሏል።
ሁለቱ ተጫዋቾች የሚገኙባቸው ክለቦችን የሚያገናኘውና በተለይ ለኢትዮጵያውያን እግርኳስ አፍቃሪያን ትልቅ ትኩረት የሚስብ በሆነው በዚህ ጨዋታ የዑመዱ ስሞሀ ቡድን በ14 ጨዋታ 19 ነጥብ በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃ ሲይዝ የጋቶች ቡድን ኤል ጎውና በ14 ጨዋታ በ15 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።