በደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት እና በካስቴል ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት በየዓመቱ የደቡብ ክልል ክለቦችን አቋሞ ለመፈተሽ የሚደረገው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የፊታችን ዕሁድ ይጠናቀቃል።
አስቀድሞ በአስር ክለቦች መካከል ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም በገንዘብ እና በዝግጅት ጊዜ ማነስ ምክንያት ቁጥራቸው ወደ ስድስት ዝቅ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲደረግ ቆይቷል። ሀምበሪቾ፣ አርባምንጭ ከተማ እና የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ ክለብ ኮንሶ ኒውዮርክ በምድብ ሀ፣ ስልጤ ወራቤ፣ ሀላባ ከተማ እና ሺንሺቶ ደግሞ በምድብ ለ ተደልድለው ከምድብ ሀ ሀበምሪቾ እና አርባምንጭ ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ስልጤ ወራቤ እና ሀላባ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ችለዋል።
ዛሬ ወደ ለፍፃሜ ለማለፍ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች 7 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ በረከት ወልደ ፃዲቅ በ27ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ስልጤ ወራቤን 1-0 አሸንፎ ማለፉን ሲያሰጋግጥ 9 ሰዓት ላይ ደግሞ ሀምበሪቾ ተስፋሁን ተሰማ በ3ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ሀላባ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ለፍፃሜ አልፏል።
ውድድሩ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ የፊታችን ዕሁድ ህዳር 2 ከቀኑ 8 ሰዓት ሀምበሪቾ ዱራሜ ከ አርባምንጭ ከተማ በሚያገናኘው ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል። ለደረጃ ደግሞ ስልጤ ወራቤ ከሀላባ ከተማ ከመዝጊያው ቀደም ብለው የሚጫወቱ ይሆናል።