የፊፋ የዓለም ክለቦች ውድድር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አስተናጋጅነት ባሳለፍነው ረቡዕ ሲጀመር ዛሬ በሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ይቀጥላል። አንደኛው ጨዋታንም ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ይመራዋል።
የኤሺያ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው የጃፓኑ ካሺማ አንትለርስ ከኮንካካፉ ቻምፒዮን የሜክሲኮው ጓድላሀራ የሚደረገው ጨዋታ ዛሬ በአል አይን ከተማ በሚገኘው ሀዛ ቢን ዘይድ ስታድየም 10;00 ላይ ይካሄዳል። ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ የሚደረገውን ጨዋታም በዓምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት ከደቡብ አፍሪካዊው ሲዌላ ዛኬሌ (ረዳት) እና ሱዳናዊው አህመድ ዋሊድ (ረዳት) እንዲሁም ብራዚላዊው ሳምፓኦ ዊልተን (4ኛ) ጋር የሚመራ ይሆናል።
የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ሁለት የፍፃሜ ጨዋታዎችን ፣ የአፍሪካ ዋንጫ፣ ቻን እና የማጣርያ ጨዋታዎችን የመራው በዓምላክ በ2018 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በአራተኛ ዳኛነት መመደቡ የሚታወስ ሲሆች በክለቦች ዓለም ዋንጫ ላይ ውድድር ሲመራ የመጀመርያው ነው።
የስድስት አህጉራት የክለብ ውድድሮች አሸናፊዎች የሆኑት ሪቨር ፕሌት (አርጀንቲና)፣ ቲም ዌሊንግተን (ኒውዝላንድ)፣ ሪያል ማድሪድ (ስፔን)፣ ጓድላሀራ (ሜክሲኮ)፣ ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ፣ ካሺማ ሐንትለርስ (ጃፓን) እንዲሁም የአስተናጋጇ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ክለብ የሆነው አል አይን የሚሳተፉበት ውድድር ረቡዕ ሲጀመር አል አይን ቲም ዌሊንግተንን በመለያ ምቶች አሸንፎ ወደ ቀጣይ ዙር አልፏል። ዛሬ ምሽትም ከአፍሪካ ቻምፒዮኑ ኤስፔራንስ ጋር ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ይጫወታል።