ከ23 ዓመት ብሔራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ አሸንፏል

ከሱዳኑ አል ሂላል አቢያድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሙሉ ብልጫ ጋር 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሶማልያ ጋር ለማድረግ ሱሉልታ ላይ ተሰብስቦ ልምምድ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ዛሬ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከሱዳኑ አል ሂላል ኦቢያድ ጋር ተገናኝቷል። ያሏቸውን ተጨዋቾች በሙሉ በጨዋታው ለመሞከር ያሰቡ የሚመስሉት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በሁለቱ አጋማሾች ሁለት ቡድኖችን የተጠቀሙ ሲሆን ከሁለቱም አንድ አንድ ግቦችን አግኝተዋል።

በጨዋታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አጥቅቶ የተጫወተ ሲሆን 10ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከፈጠረው ጫና የማዕዘን ምት አግኘቶ የማዕዘን ምቱ ሲሻማ ኳስ በእጅ በመነካቷ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እስራኤል እሸቱ ማስቆጠር ችሏል። ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ በጀመረበት ጉልበት ባያጠናቅቅም ከተጋጣሚው የተሻለ ሆኖ ታይቷል። ተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ገናናው ረጋሳ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ ፣ ታዎድሮስ ታፈሰ ፣ ዬሴፍ ዮሃንስ ፣ አቤል እንዳለ፣ አቤል ማሞ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና እስራኤል እሸቱ ጨዋታውን የጀመሩ ተጫዋቾች ነበሩ።

ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ ከፈቱዲን ጀማል እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ውጪ የቀሩትን ተጨዋቾች በፂዮን መርዕድ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ሸዊት ዮሀንስ ፣ የአብስራ ተስፋዬ ፣ ቡልቻ ሹራ ፣ አቡበከር ሳኒ ፣ በረከት ደስታ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ተክቶ ነበር ወደ ሜዳ የተመለሰው። በጨዋታውም ሙሉ ብልጫ ወስዶ የተጫወተ ሲሆን በአማኑኤል ፣ ቡልቻ እና በረከት አስደንጋጭ ሙከራዎችን አድርጓል። ሆኖም 78ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ድንቅ ብቃት ሲያሳይ የዋለው የመከላከያው አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰ በረጅም ኳስ ካስጀመረው ጥቃት የመስመር ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ ነበር ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው። ጨዋታውም በዚሁ የ2-0 ውጤት ተጠናቋል።

ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ከዛሬው ተጋጣሚው ጠንካራ ፈተና ባይገጥመውም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየው እንቅስቃሴ ለቅድመ ማጣሪያው ተስፋን የሚፈነጥቅ ሆኖ አልፏል።