የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ በሀምበሪቾ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በዱራሜ ከተማ አስተናጋጅነት ሲደረግ የነበረው የከፍተኛ ሊግ ክለቦች አቋማቸውን የሚፈትሹበት የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ከጥቅምት 24 እስከ ህዳር 2 ሲካሄድ ቆይቶ በሀምበሪቾ ዱራሜ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቋል።

ስድስት ክለቦችን ባሳተፈው በዚህ ውድድር 06:00 ላይ ለደረጃ ስልጤ ወራቤ እና ሀላባ ከተማን የሚያገናኝ መርሀ ግብር የወጣ ቢሆንም ሁለቱም ክለቦች በሜዳ ላይ ባለመገኘታቸው ምክንያት ጨዋታውን ሳይደረግ ቀርቷል። 

በመቀጠል በዱራሜ ሁለገብ ስታዲየም ለዋንጫ በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበሩት እና በምድብ ጨዋታ 1-1 የተለያዩት የአዘጋጁ ከተማ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ከፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ የወረደውን አርባምንጭ ከተማን ነው። ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት እና ጥሩ ፉክክር የተስተዋለበት ጨዋታ በሀምበሪቾ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አርባምንጭ ከተማን ለቆ ዘንድሮ ሀምበሪቾን የተቀላቀለው አጥቂው ዘካሪያስ ፍቅሬ በ58ኛው ደቂቃ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት በአግባቡ ተጠቅሞ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሽልማት ስነስርአት ሲካሄድ አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ (የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር) እና አቶ ደመላሽ ይትባረክ (የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት) በስነ ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ሽልማቶቹን አበርክተዋል። በዚህም መሠረት ኮከብ ግብ ጠባቂ ሄኖክ ወንድማገኝ ከሀምበሪቾ፣ ኮከብ ተጫዋች እንዳለ ዮሐንስ ከሀምበሪቾ እና ኮከብ አሰልጣኝ ያሬድ አበጀ በተመሳሳይ ከሀምበሪቾ ለእያንዳንዳቸው የ3 ሺህ ብር የገንዘብ እና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን ኮከብ ግብ አግቢዎች ሽልማት አንድም ተጫዋች ከሁለት በላይ ማስቆጠር ባለመቻሉ ሳይሸለሙ ቀርቷል። የምስጉን ዳኞችም ሆነ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ሽልማትም አልተበረከተም። የሀምበሪቾ ቡድን ዋንጫውን በስተመጨረሻም በመረከብ ውድድሩ ፍፃሜን አግኝቷል፡፡