3ኛው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ዛሬ ተካሄደ

ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት 3ኛው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ውድድር መነሻውን እና መድረሻውን ለቡ በማድረግ በሰላም እና ደማቅ ሁኔታተጠናቀቀ።

በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር አዘጋጅነት የተዘጋጀው ይህ ሩጫ 8 ኪ/ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን መነሻውን እና መድረሻውን ለቡ በማድረግ ከ25ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተሳትፈውበታል። በዚህ በ3ኛው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ውድድር የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሐ (ኢንጂነር) እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በጋራ በመሆን ነበር ውድድሩን ያስጀመሩት።


የሩጫው ዓላማም የክለቡን ደጋፊዎች በተለያዩ መድረኮች በማቀራረብ ቤተሰብነቱን ለማጠናከር የታሰበ ቢሆንም በዋናነት ግን ክለቡ ሊያስገነባው አስቦ የዛሬ ዓመት መሠረት ድንጋይ የተቀመጠው ስታድየሙ ግንባታ ገቢ ማስገኛ መድረክ እንዲሆን በማሰብ ነው። በዚህም ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል። 

ሦስት ሰአት በጀመረው የሩጫው ውድደር የክለቡ የልብ ደጋፊዎች ክለባቸውን ገፅታ የሚያስተዋውቁበት የተለያዩ ገላጭ ምልክቶችን በመጠቀም አስገራሚ የሆኑ ቤተሰባዊ ግኑኝነታቸውን የሚያጠናክሩ ተግባራቶች በመፈፀም ነበር ሩጫው አምስት ሰዓት ሲል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም የተጠናቀቀው።

በ2007 በተጀመረው ሩጫ በተለያዩ ምክንያቶች 2008 ሳይካሄድ  ቢቀርም በ2009 በተሳታፊ ቁጥም ሆነ በሌሎች ነገሮች የተሻለ ሆኖ ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በሁሉም ረገድ የተሳታፊ ቁጥሩን በእጥፍ በመጨመር እጅግ የተዋጣለት ውድድር ተደርጎ ተጠናቋል።