የወልዋሎ ተጫዋቾች ልምምድ አቆሙ

የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጫዋቾች በደሞዝ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ያለመሟላት ምክንያት ልምምድ አቆሙ።

በያዝነው የውድድር ዓመት በሁለቱ የመጀመርያ ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገድ በመጨረሻ ደረጃ ለመያዝ የተገደዱት የወልዋሎ ተጫዋቾች የሶስት ወር ደሞዛቸው ባለመከፈላቸው ምክንያት ዛሬ ልምምድ አቁመዋል። ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቾቹ አከባቢ ባገኘችው መረጃ ተጫዋቾቹ ጥያቄውን ማንሳት ከጀመሩ በርከት ያሉ ጊዜያት ቢቆጠሩም ቀርቦ ችግሩን ለመፍታት የመጣ አካል ባለመኖሩ ተጫዋቾቹ ይህን ውሳኔ ለመወሰን እንደተገደዱ ለማወቅ ተችሏል። ከደሞዝ በተጨማሪም የትጥቅ እጥረትም እንዳላቸው የገለፁት የክለቡ ተጫዋቾች ችግሩ በክለቡ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈም ገልፀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ክለቡን ለማነጋገር ጥረት በረናደርግም ሰፋ ያለ ማብራርያ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ የክለቡን ሃሳብ ማካተት አልቻልም።