የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጠየቀው መሰረት የትግራይ ስታድየም የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ማስተናገድ የሚያስችለውን ፍቃድ ለማግኘት እንቅስቃሴ ተጀመረ።
በ1997 በመቐለ ከተማ ልዩ ስሙ እንዳ ገብርኤል በተባለ ስፍራ የመሰረት ድንጋዩ ከተጣለ በኋላ ስራው ተጀምሮ ብዙም ሳይቆይ ስራው ተቋርጦ ለበርካታት ዓመታት ከቆየ በኋላ በ2005 በድጋሚ ስራው ተጀምሮ በ2007 በከፊል ያለቀው ይህ ስታድየም በ2007 መጀመርያ ላይ መቐለ እና ወልዋሎ ባደረጉት ጨዋታ ነበር ስራው የጀመረው።
በ2007 እስከ 2008 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ጨዋታዎች ካስተናገደ በኋላ ድጋሚ ወደ ግንባታ በመግባት እስከ 2009 መጨረሻ ድረስ የሳር ተከላ እና ሌሎች ስራዎች የተሟሉለት ይህ ስቴድየም በካፍ ፍቃድ ካገኘ ከ ሃዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ስታድየሞች በመቀጠል በካፍ ፍቃድ ያገኝ የኢትዮጵያ ስቴድየም ይሆናል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰራባት የምትገኘው የትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቐለ ከተማ ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎች ካቀፈው የትግራይ ስቴድየም በተጨማሪ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚተዳደሩ ባሎኒ ስታድየም እና ሁለት 25 ሺ ተመልካች መያዝ የሚችሉ ስታድየሞች ይዛለች።