ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናወነ

ከሶማሊያ አቻው ጋር ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም በአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን የሚያደርገው ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

ከጥቅምት 21 ጀምሮ ዝግጅቱን አጠናክሮ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ከሱዳኑ አል ሒላል ኦቢዬድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወቃል።

የቡድኑን አቅም ለማሳደግ በማሰብ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ተመስገን ካስትሮ ተካተው የነበረ ሲሆን በተጨማሪም ከንዓን ማርክነህ ከባለፈው እሁድ ጀምሮ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ መስራት መጀመሩን ለማወቅ ችለናል።

በዛሬው ጠዋት 03:30 በጀመረው የመጨረሻ ልምምድ ጊዜም ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ላይ በመሆን ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርተዋል። ከዋና ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ፣ ተመስገን ካስትሮ እና ከንዓን ማርክነህ ደግሞ ዛሬ እረፍት ተሰጥቷቸው በልምምድ ወቅት ያልነበሩ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተነግሮናል።

ነገ በ10:00 አዲስ አበባ ስታድየም የሚደረገውን የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጨዋታ ቱኒዚያዊያኑ ጉዊራት ሀይተም (ዋና) ፣ ረምዚ ሔርች (ረዳት) እና ኸሊል ሀሰን (ረዳት) የሚመሩት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የስቴዲየም የተመልካች መግቢያ ዋጋ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መደበኛ የመግቢያ ዋጋ መሠረት እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።