ዛሬ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል በተደረገ ሥነ ስርዓት የ2010 የውድድር ዓመት በኮከብነት የተመረጡ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚደረጉት ውድድሮች ጥሩ ብቃት ላሳዩ ስፖርተኞች ከ1977 ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው ሽልማት አምና በተለየ መልኩ በአንድ መድረክ ላይ መከናወን የጀመረ ሲሆን ዛሬም የ2010 ኮከቦችን ተሸላሚ አድርጓል። 03፡00 ላይ እንደሚጀመር መርሀ ግብር ተይዞለት የነበረው ሥነ ስርዓቱ 04፡40 ሲል በሰርከስ ትርዒቶች የተከፈተ ሲሆን በቅርቡ በሞት ያጣነው አሰልጣኝ ሥዩም አባተም በህሊና ፀሎት ታስቧል። በመቀጠልም የፌዴሬሽኑ ፕሬዘደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ተሸላሚዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ባሉበት የመክፈቻ ንግግር አምና የነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ዘንድሮ እንዳይደገም የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ አሳስበው ፕሮግራሙ በይፋ ጀምሯል።
የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ዋና ክፍል ከመጀመሩ በፊትም የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ተቋሙ ስለመራቸው ውድድሮች አብራርተው ሽልማቱ እነዚህ ውድድሮች እንደተጠናቀቁ መሰጠት ያልተቻለው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን ተከትሎ ውድድሮቹ በጊዜው ባለመጠናቀቃቸው እንዲሁም በጊዜው የተካሄደው ምርጫ መንዛዛት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። በመቀጠልም ዋና ፀሀፊው ሽልማቱ በሦስት የተከፈለ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የየውድድሩ ኮከቦች በፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በምስጉንነት ደግሞ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ አማካይነት ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን በውጤት የበላይ የሆኑ ክለቦች እና ተጫዋችቾችም በውጤታቸው መሰረት ተሸልመዋል።
በቅድሚያ በተሰጠው ሽልማት በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፣ ገላን ከተማ እና አርሲ ነጌሌ በደረጃቸው ተሸላሚ ሲሆኑ የአቃቂ ቃሊቲው ሳምሶን ተሾመ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኗል። በመቀጠልም ምስጉን ረዳት ዳኛ ኢሳያስ ያለው ፣ ምስጉን ዋና ዳኛ በኃይሉ ጌታቸው ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ ኄኖክ አስጨናቂ (አቃቂ ቃሊቲ) ፣ ኮከብ ግብ አግቢ ያሬድ ደርሳ (ወላይታ ሶዶ) እና ኮከብ አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ (አቃቂ ቃሊቲ) በመሆን መመረጥ ችለዋል።
የደቡብ ፖሊሱ ብሩክ ኤልያስ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ባጠናቀቀበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ደግሞ ምስጉን ረዳት ዳኛ ታምሩ አደም ፣ ምስጉን ዋና ዳኛ ዘላለም መለስ ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ዓሎ (ባህር ዳር ከተማ) ፣ ኮከብ ግብ አግቢ ብዙአየሁ እንዳሻው (ጅማ አባ ቡና) ፣ ኮከብ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ (ደቡብ ፖሊስ) ሆነው ተሸልመዋል። ከአንድ እስከ ሦስት የጨረሱት ክለቦች ደቡብ ፖሊስ ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረም በውጤታቸው ተሸላሚ ሆነዋል።
በቀጣይ የተደረገው የሽልማት ሥነ ስርዓት በሁለቱ የወጣቶች ውድድሮች ላይ የተደረገ ነበር። ሀዋሳ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ በደረጃቸው በተሸለሙበት ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማዎች የግለሰብ ሽልማቶች ላይ የበላይ ሆኗል። በዚህም መሰረት መስፍን ታፈሰ በኮከብ ተጫዋችነት እና ኮከብ ግብ አግቢነት ሲመረጥ አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ ደግሞ ኮከብ አሰልጣኝ መሆን ችሏል። በሌላ በኩል ተስፋሁን አዲሴ ከአዳማ ከተማ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሲሆን ምስጉን ረዳት ዳኛ እሸቱ ቢቂላ እንዲሁም ምስጉን ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱም ሽልማታቸውን ወስደዋል።
ወላይታ ድቻ ሙሉ ለሙሉ ሽልማቶቹን ጠራርጎ በወሰደበት የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሀብታለም ታፈሰን በኮከብ ተጫዋችነት ፣ አቡሽ አበበን በኮከብ ግብ ጠባቂነት ፣ ሳምሶን ደጀኔን በኮከብ ግብ አግቢነት እንዲሁም ግዛቸው ጌታቸውን በኮከብ አሰልጣኝነት አስመርጧል። ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ምስጉን ረዳት ዳኛ ወገን ታደሰ እንዲሁም ምስጉን ዋና ዳኛ ስለሺ ገብሬ ሌሎች የውድድሩ ተሻላሚዎች ሆነዋል።
ምስጉን ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ እና ምስጉን ዋና ዳኛ ፀሀይነሽ አበበ በተሸለሙበት የሴቶች ሊግ ዘርፍ በአንደኛ ዲቪዚዮን ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ በደረጃቸው ተሸልመዋል። የደደቢት ተጫዋቾች አጠቃለው በወሰዷቸው ሽልማቶችም የኢቢሲ ስፖርት ሽልማትን ያገነችው ሰናይት ቦጋለ ኮከብ ተጨዋች ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ ገነት አክሊሉ ፣ ኮከብ ግብ አግቢ ሎዛ አበራ ኮከብ አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም በመሆን አሸንፈዋል።
ጥረት ኮርፖሬት ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ከአንድ እስከ ሦስት በመሆን በተሸለሙበት የሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ምስር አብርሀም ከጥረት ኮርፖሬት ኮከብ ተጫዋች ሆና ስትመረጥ የቡድን አጋሯ ታሪኳ በርገና ኮከብ ግብ ጠባቂ ፣ አሰልጣኝ ሠርክአዲስ ትዕግስቱ ደግሞ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነዋል። በሌሎች ሽልማቶች ፎዚያ መሀመድ (ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ) እና ምስር አብርሀም (ጥረት ኮርፖሬት) ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ችለዋል።
የመጨረሻ በነበረው ኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባ ጅፋር ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና እንደደረጃቸው ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ተመስገን ሳሙኤል እና ብሩክ የማነብርሀን የምስጉን ረዳት ዳኛ እና የምስጉን ዋና ዳኛ ክብርን አግኝተዋል። በኮከቦች ሽልማት ደግሞ የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት አሸናፊው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሀመድ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ሲመረጥ የጅማ አባ ጅፋሮቹ ዳንኤል አጄዬ ኮከብ ግብ ጠባቂ ፣ ኦኪኪ አፎላቢ ኮከብ ግብ አግቢ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ደግሞ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን አሸንፈዋል።
እንደ ቢጫ እና ቀይ ካርድ ቁጥር ባሉ የዲስፕሊን ሪከርዶች ላይ ተመስርቶ በሚደረገው የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ጅማ አባ ጅፋር ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ እና ጥረት ኮርፖሬት ደግሞ ከአንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነው የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያ ወልዋሎ ዓ.ዩን ባስተናገደበት ጨዋታ በተነሳው ግርግር ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴን ከጥቃት ለመከላከል ጥረት ያደረገው ፍፁም ገብረማርያም የስፖርታዊ ጨዋነት ልዩ ተሸላሚ መሆን ችሏል።