አስተያየት | በዘርዓይ ኢያሱ |
የፊታችን እሁድ ኢትዮጵያ ለ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋናን በአዲስ አበባ ስታድየም ታስተናዳለች፡፡ በመጀመሪያ ጨዋታ በጋና 5ለ0 የተሸነፈችው ኢትዮጵያ በኬን ያ ደግሞ 3ለ0 መረታቷ የሚታወስ ነው፡፡ የኬንያው ሽንፈት ለእሁዱ ጨዋታ የሚሰጠው ጥቆማ ስላለ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ሞክሪያለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ባደረገችው የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ 3ለ0 ስትሸነፍ ሶስቱም ጎሎች የተቆጠሩበት መንገድ ከመከላከል ጋር በተያያዘ የታዩት ክፍተቶች ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ይህንን ትንታኔ ለመስራት የሁለቱን ሃገራት ጨዋታ ተንቀሳቃሽ ምስል (video) በድጋሚ በጥልቀት ስመለከት ብዙ ሊተነተኑ የሚገባቸው ነጥቦችን አግኝቻለሁ፡፡ እንደተለመደው ሁሉ ከታክቲክ ጋር በተያያዘ በጣም ብዙ ክፍተቶች ያየሁበት ጨዋታ ቢሆንም ለዚህ ፅሁፍ ይረዳኝ ዘንድ ሶስቱ ጎሎች ሲቆጠሩ የሰራናቸው ስህተቶች ላይ ለማተኮር ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይ በቅጡ አለመከላከል ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ምን እንደሆነ እንዲሁም የአማካዮቹ ከማጥቃት ወደ መከላከል የነበረው ሽግግር አነስተኛ መሆን አሁንም ብሄራዊ ቡድኑ በቀላሉ ከሚሸነፍባቸው ምክንያች መካከል አንዱ ሆኖ ያልተፈታ ችግር መሆኑን ቀጥሏል፡፡
የመጀመሪያዋ ጎል (ግብ ጠባቂውን አለመከላከል)
በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያዋ ጎል በ23 ደቂቃ ስትቆጠርብን በቅብብሎሹ ተሳትፎ የነበራቸው ሶስት የኬንያ ተጨዋች ብቻ ናቸው፡፡ ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ በረጅሙ የላካት ኳስ ለማይክል ኦሉንጋ ከደረሰች በኋላ ኦሉንጋ ከኤሪክ ጆሃና (10) ጋር ተቀባብሎ አስደናቂ ግብ ከርቀት አስቆጥሮ ኬንያን መሪ አደርጋት፡፡ ኢትዮጵያ ይህቺ የመሪነት ጎል ሲቆጠርባት ዋነኛ ድክመት የነበረው የማጥቃት ሂደቱ የሚጀምርበትን ቦታ መከላከል አለመቻል ነው፡፡
በሌላ አባባል በዚህች ጎል መቆጠር ሂደት ውስጥ በተጋጣሚ የመከላከል ዞን ውስጥ የነበሩ ወይም በግብ ጠባቂው አቅራቢያ የነበሩ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ፓትሪክ ማታሲ በረጅሙ እንዳይለጋ አለመከላከላቸው ነው፡፡ ምናልባት ይህ ቢሆን ኖሮ የግብ ጠባቂውን ሃሳቡ ማስቀየር አልያም ማዘግየት ይቻል ነበር፡፡ ውሳኔውን ማዘግየት ወይም ደግሞ ሃሳቡን አስቀይሮ ቢሆን ኖሮ መደበኛ ቦታቸውን ለቀው የነበሩ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ተደራጅተው በጥሩ ሁኔታ መከላከል ይችሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለግብ ጠባቂው ቅርብ የነበሩት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች አፈግፍገው የነበረ በመሆኑ ፓትሪክ ማታሲ ማድረግ የሚገባውን አድርጎ የመሪነቷንና 60 ሺ ተመልካቾችን ያስፈነደቀችዋን ጎል አስቆጠሩ፡፡
ሁለተኛዋ ጎል (የመደራጀት ችግር)
በይበልጥ ኬንያውያንን በራስ መተማመን ከፍ ያደረገችው ሁለተኛ ጎል ስትቆጠር መነሻዋ ቅጣት ምት መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ አስቻለው ታመነ በኬንያው ተጨዋች ፍራንሲስ ካሃታ ላይ በፈፀመው ጥትፋ የተሰጠችውን ቅጣት ምት ወደ መስመር ተልካ ከዚያም ወደ ጎል ተሻማች፡፡ ይህችኑ ኳስ አስቻለው ታመነ በግንባሩ ገጭቶ ቢያወጣትም ብቻውን በጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረው 10 ቁጥሩ ኤሪክ ጆሃና በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ሃገሩን ሁለት ለዜሮ እንድትመራ አደረገ፡፡ ታዲያ ይህቺ ኢትዮጵያን ተስፋ ያስቆረጠች ጎል ስትቆጠር ስህተቱ የማን ነበር እንዴትስ መከላከል ይቻል ነበር የሚለውን እንመለከት፡፡
አስቻለው ታመነ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የእለቱ የመሃ ዳኛ ቅጣት ምት ስለሰጡ ጨዋታው ለሰንከዶች ያህል ቆሞ ነበር፡፡ ጥፋቱ ኬንያ ቅጣት ምት እንድታገኝ ቢያደርጋትም በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ደግሞ ጥቅም ነበረው፡፡ ጥቅሙ ምንድነው ያላችሁኝ እንደሆነ በቅጣቱ ምክንያት ጨዋታው ለሰከንዶች ያህል መቆሙ የእኛ አማካዮች በፍጥነት ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተደረጃተው መከላከል እንዲችሉ ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩ ነው፡፡ ይህ ማለት አማካዮች በፍጥነት ወደ ኋላ በማፈገፈግ ከተከላካዮቹ ጋር ያላቸውን ርቀት ማጥበብ ማለት ነው፡፡
ይህ በሚሆንበት ግዜ በአማካዮቹና በተከላካዮቹ መካከል ያለውን ቦታ በማጥበበብ የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋች ከመስመር የሚሻገሩ ኳስች አደጋ እንዳይፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የእኛ አማካዮች በተለይም የአማካይ ተካለካዮቻችን በዚህ በኩል ከፍተኛ ክፍተት የነበረባቸው ሲሆን በመከላከል ግዜ ትክክለኛው ቦታ ላይ አለመገኘት ለጎሉ መቆጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ በቅጣት ምት የተጀመረው ኳስ ወደ መስመር ወጥቶ ከመስመር ሲሻማ ከላይ እንደጠቀስኩት አስቻለው ታመነ በግንባር ገጭቶ ቢያወጣውም ኳሷ ብቻውን ለነበረው ለኤሪክ ጆሃና ደረሰችና በጥሩ ሁኔታ አስቆጠረ፡፡ ይህ በሚሆንበት ግዜ በተከላካዮቹና በአማካዮቹ መካከል በግምት 10 ሜትር በላይ ርቀት ነበር፡፡
በዚህ ክፍት ቦታ የነበረው ኤሪክ ጆሃና ግቧን ከማስቆጠሩ በፊት በዚህ ቦታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መገኘት የነበረባቸው ሁለቱ የአማካይ ተከላካዮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የመሃል ተከላካዮቹ ከመስመር የሚሻሙ ኳሶችን ለመከላከል ወደ ግብ ጠባቂው በጥልቀት ሲገቡ ከፊት ለፊታቸው ሰፊ ቦታ ጥለው ይሄዳሉና፡፡ለዚህም ነው ኤሪክ ዮሃና ከተከላካዮቹ በፊት ያለውን ክፍት ቦታ ከመጠቀሙ በፊት የመከላከሉ ሃላፊነት የእነሱ ነበር፡፡ ነገር ይህ ባለመሆኑ ቡድኑ ተጨማሪ ጎል ለማስተናገድ ተገዷል፡፡
ሶስተኛ ግብ (23 ቅብብሎሽ)
በሁለተኛው ግማሽ 45 ደቂቃ የተቆጠረብን ጎል አንድ ብቻ ቢሆንም ኬንያ ግን በኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ብላጫ ነበራት፡፡ በጎሎችና በበርካታ ሙከራዎች ያልታገዘ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በራሱ ስኬት ነው ብሎ መውሰድ ባይቻልም ኬንያ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ከማስቆጠሯ በፊት የነበረው የኳስ ፍሰት ማራኪና ድንቅ ነበር፡፡ አህመድ ረሺድ በኤሪክ ጆሃና ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አንበሉ ቪክቶር ዋኒያማ ከማስቆጠሩ በፊት የኬንያ ተጨዋች 23 ግዜ (አንዱ ተጨዋች ደግሞ የነካው ሳይቆጠር) ተቀባብለዋል፡፡
ይህቺ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ከመቆጠሯ በፊት የኳሳ መነሻ የት ነበር የሚለውን እንመልከት፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ ከመገኘቱ በፊት ኳሷ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የተሻማችው ከግራ መስመር ነው፡፡ በግዜው የግራ መስመር ተከላካይ ሆኖ የተጫወተው አህመድ ረሺድ ወደ ውስጥ አጥብቦ የነበረ በመሆኑ የተሻማው ኳስ በቀጥታ የደረሰችው ኤሪክ ጆሃና ጋ ነበር፡፡ ተጨዋቹም በአህመድ ረሺድ በመጠለፉ ኬንያ በፍፁም ቅጣት ምት ሶስተኛ ጎል አስቆጥራ 3ለ0 አሸንፋለች፡፡ በእለቱ ጨዋታ ሶስት ጎሎች ሲቆጠሩብን ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኳቸው ሶስት ነጥብች ዋነኛ ችግሮቻችን ነበሩ፡፡
የጋና የጨዋታ ስልት
የጋና የማጥቃት ስልት wide attack ሜዳ አስፍቶ መጫወት ነው፡፡ ይህንን ስልት ለመጠቀም 4-3-3 የጨዋታ ፎርሜሽንን የሚጠቀሙ ሲሆን ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ መስመር ይወጣሉ፡፡ በዚህ ሚና ውስጥ የአማካዮቹ፤ የመስመር አጥቂዎቹና የመስመር ተከላካዮቹ ጥምረት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
በይበልጥ ግን በአማካዮቹና በመስመር አጥቂዎቹ መካከል የሚኖረው ጥምረት ስልቱን ውጤታማ ለማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነ እነሱም በዚህ መንገድ ሊመጡ እንደሚችል በመገመት ይህ ጉዳይ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ስንሸነፍ በግራ በኩል (ስንከላከል በቀኝ በኩል ማለት ነው) የማጥቃት ሚዛን ነበራቸው፡፡
በተለይ ደግሞ የግራ መስመር አማካዩ ቶማስ አግዮፓንግ (7 ቁጥር) በጥልቀት ማጥቃት ላይ የነበረው ተሳትፎ እጅግ አደገኛ በመሆኑ ጋና ብዙ ጎሎችን እንድታስቆጥር ምክንያት ሆኗል፡፡
ከአምስቱ ጎሎች አራቱ መነሻቸው ከዚሁ ስፍራ መሆናቸው እንደ ምሳሌ ሊታይ ይችላል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የጋና የማጥቃት ስልት wide attack ሜዳ አስፍቶ መጫወት ነው፡፡ የማጥቃት ሚዛኑም በግራ በኩል ዘንበል ይላል፡፡ ይህ ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ወደ ቀኝ ሊያመዝኑ እንደሚችልም መገመት ያስፈልጋል፡፡
ማጠቃለያ
ከዝርዝር ፅሁፉ የምንረዳው ኳስ በያዘው ተጨዋች አቅራቢያ ያለው የኢትዮጵያ ተጨዋች በተለያዩ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የጨዋታው ሂደት ከመጀመሩ በፊት ለመከላካል ያላቸው ዝግጁነት አልያም ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡
ስለሆነም የመከላከል ስራ የተከላካዮች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተጨዋች መሆኑን መገንዘብ የሚያስችለን እውነታ ነው፡፡
*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡
*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com