የኢትዮጵያ እግርኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስለነገው ጨዋታ ያላቸውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።
ነገ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋውን ለማለምለም እጅግ ወሳኝ የሆነውን አምስተኛ የምድብ ጨዋታ ከጋና አቻው ጋር ያደርጋል። ቡድኑ ለዚህ ጨዋታ ዛሬ 04፡00 ላይ የመጨረሻ ልምምድ ካደረገ በኋላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱም ስለቡድናቸውን እና ስለጨዋታው በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ያላቸው ሀሳብ እንደሚከተለው አካፍለውናል።
ስለዝግጅት ጊዜ…
ዝግጅታችን በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነበር። ከሊጉ መቋረጥ ጋር ተያይዞ ጥቅምት 27 ነበር የጀመርነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ የተጫዋቾችን የአካል ብቃት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ለማድረስ በማሰብ ከተወሰነ የታክቲክ ስራ ጋር ያያ ቪሌጅ ሱሉልታ ላይ የሰራነው ነበር። ሁለተኛው ደግሞ አዲስ አበባ ስታድየም እና አካዳሚ ሜዳ ላይ በቅንጅት እና ከአጨዋወት መንገዳችን ጋር የተገናኙ ስራዎችን ስንሰራ የቆየንበት ነው። ጥሩ የዝግጅት ጊዜ እንደነበረንም አስባለሁ።
የ23 ዓመት ብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተመሳሳይ የዝግጅት ጊዜ መኖሩ ሊፈጥር ስለሚችለው የትኩረት ችግር…
በዕቅድ የምትመራ ከሆነ ችግር የለውም። ባወጣነው ዕቅድ መሰረት ቀድመን የተዘጋጀን በመሆኑም መስመር ይዞ እየሄደ ነው። በተጨማሪም ብቻዬን አይደለውም። አብዛኛውን ኃላፊነት ሙሉጌታ ፣ ውብእሸት እና ፋሲል በአግባቡ በመወጣታቸው ብዙም ከባድ አልነበረም። የኦሊምፒክ ቡድኑ ሰኞ ወደ ጅቡቲ ሲሄድም የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱም የምንኖር ይሆናል።
ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር የነበረው የመጀመሪያው ጨዋታ ውጤት ተፅዕኖ…
የመጀመሪያው ጨዋታ 5-0 የተጠናቀቀ ነበር። ያ የፈጠረው ጠባሳ ከተጫዋቾቹ አዕምሮ ውስጥ መውጣት ስለነበረበት በውጤቱ ወደ ቁጭት ስሜት እንዲገቡ የተደረገ የሥነ ልቡና ዝግጅት አለ። ከዛ በተጨማሪም በሀገራችን ያሉ ስመጥር የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ከቡድናችን ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል። ስለዚህ ይህ ጨዋታ እንደ አዲስ ምዕራፍ ይሆናል ማለት ነው።
ጉዳቶች…
ጌታነህ እና አምሳሉ ጉዳት አለባቸው። አሁነሠ ከጉዳቱ አገግመዋል ፤ ጥሩ ናቸው። ነገር ግን ከጉዳቱ ጋር በተያያዘ ሊሰሩ የሚገባቸው የአካል ብቃት ስራዎች እና የቅንጅት ስራዎችን ስላልሰሩ ብቻ ከነገው ስኳድ ውጪ የሆኑት። በተረፈ ሌሎቹ ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ጌታነህ የቡድኑ አምበል እንደመሆኑ እሱን ተክተው የሚገቡ ተጫዋቾችን የሚያበረታታ ይሆናል። እነርሱም ጥሩ ነገር እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለው።
የአጨራረስ እና ዕድል የመፍጠት ችግር…
የብሩንዲው ፣ የሴራሊዮኑ እና የባህር ዳሩ የኬንያ ጨዋታ ላይ ኳሶች ተስተዋል። ይህንን ለመቅረፍም ለአጥቂዎቻችን እና ከአጥቂዎቻችን ጀርባ ለሚጫወቱ የማጥቃት ባህሪ ላላቸው አማካዮቻችን የተለዩ ልምምዶችን ስንሰጥ ቆይተናል። ነገር ግን ችግሩ በዚህ ፍጥነት ሙሉ ለሙሉ የሚቀረፍ አይደለም። ተደጋጋሚ ስራዎችን ይጠይቃል ፤ ችግሩ ከታች ተያይዞ የመጣ ስለሆነ ማለት ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ድክመታችን ስለነበር ያንን ድክመት ለመቀነስ በዚህች አስራ ሁለት ቀናት ውስጥ ማድረግ ያለብንን ሁሉ አድርገናል። በመሆኑም የተሻለ ነገር እንደሚኖር ተስፋ እናደርጋለን።