ሪፖርት | ዋሊያዎቹ በሜዳቸው በጋና ተሸንፈዋል

በ2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አምስተኛ የምድብ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጋናን አስተናግዶ በመጀመሪያው አጋማሽ ጆርዳን አዬው በጨዋታና በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ የማለፍ ተስፋውን በእጅጉ አጨልሟል፡፡

ዋልያዎቹ ባሳለፍነው ወር ወደ ኬንያ አቅንቶ በኬንያ ብሔራዊ ቡድን 3ለ0 ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ የ7 ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። ከነዚህም ቅያሬዎች መካከል የመከላከያው የመሀል ተከላካይ አበበ ጥላሁን ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያውን ጨዋታ ሲያደርግ ዑመድ ኡክሪም ወደ መጀመርያ ተሰላፊነት ተመልሶ የፊት መስመሩን እየመራ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ በአንጻሩ በጋና ብሔራዊ ቡድን በኩል ዳግም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ በአዲስ መልክ የተካተቱት ጆርዳንና አንድሬ አዬው በዛሬው ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው ሲጀምሩ አምበሉ አሳሞሃ ጂያን በተቃራኒው በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ነበር ጨዋታውን የጨረሰው፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ጋናዎች የመጀመሪያ ግባቸውን ያገኙት ገና በጊዜ ነበር ፤ በ3ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው እጅግ ድንቅ የነበረው የጋናው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሀሪሰን አፉል ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅሙ ያሳለፈለትን ኳስ በደስታ ዮሀንስና አበበ ጥላሁን የትኩረት ማጣት ኳሷን በቀላሉ ያገኘው ጆርዳን አዬው ኳሷን ከጠበበ አንግል በግሩም ሁኔታ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጠራ የግብ እድሎችን ለመፍጠር በተቸገረበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለት አጋጣሚዎች ምንይሉ ወንድሙ በመልሶ ማጥቃት በተገኙ አጋጣሚዎች ወደ ግብ የላካቸው ኳሶች ብቻ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

 

ጋናዎች ኳስን በሚቆጣጠሩበት ወቅት በፍጥነት ፈጣን ለሆኑት ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች አንድሬ አዬውና ክሪሴትያን አትሱ ኳሶችን በማድረስ በተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በ22ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች አደገኛ ቀጠና ላይ በሰሩት ስህተት ጋናዎች ያገኙትን ኳስ ሙባረክ ዋካሶ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ይዞ ለመግባት ሲሞክር አበበ ጥላሁን በሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጆርዳን አየው ዳግም አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በጋና ተጫዋቾች በቀላሉ ጫና ሲያሳድሩባቸው በበርካታ አጋጣሚዎች በአደገኛ ቀጠናዎች ውስጥ ኳሶችን ሲሳሳቱ ተስተውሏል ነገርግን እንደ እድል ሆኖ በተመሳሳይ መንገድ ግቦችን ሳያስተናግዱ ቀርተዋል፡፡ በ41ኛው ደቂቃ ላይ አበበ ጥላሁን ከጋና ተከላካዮች ጀርባ በግሩም ሁኔታ ለአብዱልከሪም መሀመድ ያሳለፈለትን ኳስ አብዱልከሪም በጥሩ ሁኔታ ከተቆጣጠረ በኃላ ከአዲስ ግደይ ለማቀበል የሞከረውና የጋና ተጫዋቾች ያቋረጡበት ኳስ በኢትዮጵያ በኩል የመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር፡፡

ከእረፍት መልስ ዋሊያዎቹ በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፤ በመጀመሪያው አጋማሽ የ2ለ0 የበላይነት ይዘው ወደ መልበሻ ቤት ያመሩት ጋናዎች በመጠኑ ወደ ኃላ ለማፈግፈግ ምርጫ ማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ ተሽሎ ለመቅረቡ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

ዋሊያዎቹ በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻሉ ይሁኑ እንጂ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የግብ እድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ ምንይሉ ወንድሙ በግንባር ገጭቶ የሞከራትና የጋናው ግብጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም ዑመድ ኡኩሪ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

ጨዋታው በጋና ብሔራዊ ቡድን 2ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዋሊያዎቹ ካረጓቸው 5 ጨዋታዎች ሶስቱን ተሸንፈው በአንዱ አሸንፎ በአንዱ አቻ በመውጣት በአራት ነጥብ በምድቡ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ