የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን ዛሬ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሲጀመር ሀዋሳ ከተማ፣ ጌዲኦ ዲላ እና አዳማ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ዓመቱን በድል ከፍተዋል፡፡
የጸጥታ አካላት በስታዲየሙ ባለመኖራቸው ከተያዘለት ሰዓት 25 ያህል ደቂቃዎችን ዘግይቶ በጀመረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም በሆነ የጨዋታ ብልጫ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ያደገው ጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች አካዳሚን 5-0 በመርታት ዓመቱን በድል ጀምሯል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሳቢ ባልሆነው እንቅስቃሴ ምርቃት ፈለቀ ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ በ14ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥራ ሀዋሳን ቀዳሚ ማድረግ ስትችል በ41ኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ ለራሷና ለቡድኗ ሁለተኛ ግብን በ41ኛው ደቂቃ አስቆጥራ በሀዋሳ 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ተደጋጋሚ የማጥቃት ኃይልን ተጠቅመው ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የተንቀሳቀሱት ሀዋሳዎች 59ኛው ደቂቃ በነፃነት መና፣ 64ኛው ደቂቃ ተከላካይዋ ነፃነት መና እና 85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቅድስት ቴካ አክርራ የመታችው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፋ ግብ ብትሆንም ጎሏ በቅድስት ተመዝግቦ ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተደምድሟል፡፡
ዲላ ላይ ጌዲኦ ዲላ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት ዓመቱን በድል የጀመረ ሌላኛው ክለብ ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ስራ ይርዳው ባስቆጠረችሁ ግብ እየመራ የዘለቀ ቢሆንም ከእረፍት መልስ ስመኝ በረዲ እና ከአዳማ ከተማ ጌዲኦ ዲላን የተቀላቀላቀለችው ድንቅነሽ በቀለ ደግሞ ሌላኛው ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በባለሜዳው ጌዲኦ ዲላ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዳማ ላይ መከላከያን የገጠመው አዳማ ከተማ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ለአዳማ የድል ግቦቹን ሰርካዲስ ጉታ እና ከጌዲኦ ዲላ አዲስ የፈረመችው አጥቂዋ ሳራ ነብሶ ሌላኛውን ግብ ስታክል መከላከያን ከሸንፈት ያልታደገችውን ግብ የምስራች ላቀው አስቆጥራ በአዳማ ከተማ 2-1 የበላይነት ተጠናቋል።
ነገ ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ አዲስ አበባ ከተማ ከጥረት ኮርፖሬት፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ በሚደረጉ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች የሚቀጥሉ ይሆናል።