የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በየአመቱ የሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በአምበር ቢራ ስም ይካሄዳል፡፡

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት 6 የአዲስ አበባ ክለቦች እና ሁለቱ ተጋባዥ የክልል ክለቦች በአምናው ውድድር ላይም የተሳተፉት በመሆኑ የተሳታፊ ቡድን ለውጥ የለም፡፡ በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኤሌክትሪክ ፣ መከላካያ ፣ ኢትየጵያ ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት ፣ አዳማ ከነማ እና ዳሽን ቢራ በ2008 ውድድር ላይ ይሳተፋሉ፡፡

ዛሬ በ5፡00 ላይ 4 ኪሎ በሚገኘው የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር አዳራሽ በወጣው የምድብ ድልድል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የምድብ አባት ሆነዋል፡፡ የምድብ ድልድሉ የሚከተለው ነው፡፡

ምድብ ሀ

ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ዳሽን ቢራ እና ደደቢት

ምድብ ለ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መከላከያ ፣ አዳማ ከነማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ፌዴሬሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዳስታወቀው አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በቀር ሁሉም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋሉ፡፡ በመክፈቻ ጨዋታው ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም በ9፡00 ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት ጨዋታ የሚያደርጉ ሲሆን በዚሁ ምድብ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ዳሽን ቢራ በ11፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ የምድ 2 ጨዋታዎች የሚደረጉት ከ3 ቀናት በኋላ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓም ሲሆን በ9፡00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ በ11፡00 ደግሞ መከላከያ ከ አዳማ ከነማ ይጫወታሉ፡፡

የሽልማት ክፍፍል

ፌዴሬሽኑ ከሜዳ ገቢ የሚገኘውን ገቢ ለስድስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች የሚያከፋፍል ሲሆን ተጋባዦቹ ክፍፍሉ አይመለከታቸውም፡፡ ከስፖንሰር ሺፕ የተገኘው ገንዘብም በክፍፍሉ ውስጥ አይካተትም፡፡

የክልል ክለቦች የፍፃሜ ጨዋታ ቢያሸንፉ እንኳን ዋንጫው የተሻለ ደረጃ ላለው የአዲስ አበባ ክለብ ሲሰጥ ለአሸናፊው የክልል ክለብ በዋንጫው ምትክ ልዩ ሽልማት ይበረከትለታል፡፡ የክፍፍሉ መጠን በመቶኛ ይህንን ይመስላል፡-

 

1ኛ – ከሜዳ ገቢ 15%

2ኛ – 10%

3ኛ – 10%

4ኛ – 4%

5ኛ – 3%

6ኛ – 3%

ውድድሩ ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል፡፡

ያጋሩ