በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ አሸንፈዋል

በትላንትናው እለት የተጀመረው የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ዛሬ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። 

09:00 ላይ ዘንድሮ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ እና ጥረት ኮርፖሬት ያደረጉት ጨዋታ በመዲናው ክለብ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ጥረቶች ገና በ4ኛው ደቂቃ ምስር አብርሀም ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ከጎሉ በኋላም ተጨማሪ የግብ እድሎች መፍጠር ችለው ነበር። 



ሆኖም ቀስ በቀስ የጨዋታ የበላይነት መያዝ የቻሉት አዲስ አበባዎች የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰኮንዶች ሲቀሩ አቻ መሆን ችለዋል። በጨዋታው ጥሩ  የተንቀሳቀሰችው ፍቅርተ ብርሀኑ ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት የጥረቷ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና ስህተት ታክሎበት ከመረብ አርፎ በአቻ ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል። 



ከእረፍት መልስም የተሻለ የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ አዲስ አበባዎች ሲሆኑ በተለይ ወጣቷ አጥቂ ፎዚያ መሐመድ ፍጥነቷን ተጠቅማ በተደጋጋሚ አስደንጋጭ ሙከራዎችን በማድረግ ተከላካዮችን መፈተን ችላለች። በ52ኛው ደቂቃም የማሸነፍያውን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 



11:00 ላይ አምና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አምና 9ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ቢወርድም በደደቢት ሴቶች ቡድን መፍረስ ምክንያት ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገናኘው ጨዋታ በስፍራው የተገኘው ተመልካችን ቀልብ በገዛ ፉክክር ታጅቦ በባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ረሒማ ዘርጋ በ13ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ መሆን የቻሉተ ንግድ ባንኮች ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም የኋላ ኋላ በኤሌክትሪክ ተፈትነው አምሽተዋል። በተለይ በ52ኛው ደቂቃ ረሒማ ዘርጋ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራ የባነክን መሪነት ማስፋት ከቻለች በኋላ የኤሌክትሪኮች ጫና ከፍ ብሎ ታይቷል። 



ከአካዳሚ ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀለችው መሣይ ተመስገን በ62ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪክን ወደ ጨዋታው የመለሰች ጎል ስታስቆጥር ከግራ መስመር እየተነሳች ተደጋጋሚ አደጋዎችን ብትፈጥርም ባንኮች ልምዳቸውን ተጠቅመው የ2-1 መሪነታቸውን በማስጠበቅ ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል። 


የአንደኛ ዲቪዝዮኑ የመጀመርያ ሳምንት ቀሪ አንድ ጨዋታ በቀጣይ ሳምንት የሚከናወን ይሆናል።