የሴቶች ብሄራዊ ቡድን የቡርኪናፋሶ ጉዞ አሁንም አጠራጣሪ ነው

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ከቡርኪናፋሶ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ ሊስተጓጎል ይችላል፡፡

ካፍ ጨዋታው ቅዳሜ እንዲደረግ ቢያዝም ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦጋዱጉ ሊያደርገው የነበረውን በረራ ሰርዟል፡፡ በዚህም ምክንያት ቡድኑ ወደ ኦጋዱጉ የሚያደርገው ጉዞ ላይ እክል እንደሚፈጥር በመግለጽ ካፍን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ደብዳቤ መላኩን የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

የሴቶች ወጣት ቡድኑ አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው ጨዋታውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ከከሰአቱ ልምምድ በኋላ የፌዴሬሽኑ ሰዎች አየር መንገዱ በረራ እንዳቋረጠ ነግረውኛል፡፡ አሁን ደግሞ እንደገና ተጀምሯል እየተባለ ነው፡፡ ቁርጣችንን ባናውቅም ተጫዋቾቼ ለመጫወት ዝግጁ ናቸው፡፡

‹‹ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት፡፡ ተከራክረን ጨዋታውን ወደ ፎርፌ ማስለወጥ ነበረብን፡፡ መጫወት አለመጫወታችንን መወሰን የሚችሉት አስተዳደሮቹ ናቸው፡፡ ነገሮች ተስተካክለው ተጫወቱ ከተባልን ግን ዝግጁ ነን፡፡ ››

የኢትዮጵያ እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው ከ1 ሳምንት በፊት ቢሆንም በሃገሪቱ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ካፍ ጨዋታው በመጪው ቅዳሜ እንዲደረግ ወስኖ ነበር፡፡ ጨዋታው መራዘሙን ተከትሎ ለእረፍት ተበትኖ የነበረው ብሄራዊ ወጣት ቡድናችን ትላንት በድጋሚ ተሰባስቦ ልምምድ መስራት የጀመረ ሲሆን ወደ ቡርኪና ፋሶ ለመብረር ፕሮግራም የያዘው ነገ ነበር፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ በመጀመርያው ማጣርያ ከካሜሩን አቻው ጋር 0-0 አቻ ተለያይቶ ሲመለስ በካሜሩን አየር ማረፍያ ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰበት የሚታወስ ነው፡፡

ያጋሩ