‹‹ …. ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ ቡናን ስታድየም አታዩትም ›› መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

ዛሬ ከ3፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር ኢትዮጵያ ቡና የሬድዮ ፕሮግራም የጀመረበትን 1ኛ አመት በአል ከደጋፊዎቹ ጋር አክብሯል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ንግግሮች ፣ የእውቅና ሰርተፍኬት የመስጠት ስነስርአት እና የ2008 አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች የማስተዋወቅ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ ከሁሉም የበለጠ ትኩረትን ያገኘው ግን በሳምንቱ አጋማሽ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊጉን የስያሜ መብት ለካስቴል ቢራ መሸጡን አስመልክቶ የቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የተናገሩት ንግግር ነው፡፡ ስሜታዊ በሆነና ሃይለቃላት የነበሩበት የመቶ አለቃው ንግግር የፕሮግራሙን አመዛኝ ሰአት ወስዷል፡፡

መቶ አለቃ ፈቃደ ከተናገሩት መካከል ዋና ዋናዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

‹‹ በመጀመርያ ፌዴሬሽኑ ክለቦችን ሳያማክር በማን አለብኘነት የስርጭት መብት ስምምነትን ከኢቢሲ ጋር ፈፅሟል፡፡ አሁንም ክለቦችን ሳያማክር የሊጉን ስያሜ መብት ለአንድ የቢራ ፋብሪካ ሽጠውታል፡፡ ( መቶ አለቃ ካስቴል ቢራን ጠቅሰው ማውራት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል)፡፡ ለአርቡ ውይይት ከፕሬዝዳንቱ ተደውሎ የተጠራነውም ረቡእ ነው፡፡ ››

‹‹ በአንድ ቀን ውስጥ ወስኛለው ብለው ተግባራዊ ይደረግ ማለት ሳይሆን ቅድሚያ ክለቦችን አናግሮ ወደ ውሳኔ መድረስ ነበር የነበረባቸው፡፡ የሊግ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከወር በፊት ለፌዴሬሽን ደብዳቤ አስገብተን ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ምላሽ አልተሰጠንም፡፡ ይህ አይነት ስምምነት ደግሞ ክለቦች በሚያስተዳድሩት ሊግ ኮሚቴ ስር ነው፡፡››

‹‹ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አንሳተፍም ስንል የነበረው ቅድሚያ የውድድር ፕሮግራሙን ማወቅ ስለነበረብን ነው፡፡ አሰልጣኛችን የውድድር ፕሮግራሙን አምጡና ቡድኔ መሳተፍ አለመሳተፋችሁን እንወስናለን ብሎን ነበር፡፡ ቡድናችን ለአዲሱ የውድድር ዘመን እያዘጋጀን ስለሆነ በመሃል በሚደረግ ውድድር ጊዜ ማጥፋት አልፈለግንም፡፡ ከውድድሩ ዋንጫ ፈልገን ሳይሆን ስለተጠራን ብቻ ነው የምንሳተፈው፡፡ ››

‹‹ ስለ ብሄራዊ ቡድን እና ክለቦች ግንኙነት በመተዳደርያ ደንቡ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ይህንን ተከትሎ መስራት አልቻለም፡፡ ተጫዋቾችን በፈለጉበት ጊዜ እየጠሩ በሆቴል እያስቀመጡ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፌዴሬሽኑ በፋይናንሱ ይከስራል፡፡ ከለቦችም እየከሰሩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ትግላችን ይቀጥላል፡፡ ››

‹‹ የክለባችንን ስፖንሰሮች እናከብራለን፡፡ በሜዳችን በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ከሀበሻ ቢራ ጋር በተስማማነው መሰረት ስፖንሰራችንን በሜዳ ውስጥ እናስተዋውቃለን፡፡ ፌዴሬሽኑ ውል የገባው ከተመሳሳይ ምርት ጋር በመሆኑ እኛ ይህንን ተቃውመናል፡፡ የማይስተካከል ከሆነም ቡናን ስታድየም አታዩትም፡፡ የፕሪሚየር ሊጉን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫንም ከኛ ስፖንሰር ጋር ተመሳሳይ ምርት ነው ስፖንሰር ያደረገው፡፡ ››

ያጋሩ