በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያን የሚወክለው ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ቴሌኮም ጋር የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን የፊታችን ማክሰኞ ጅቡቲ ላይ ያደርገል። የቡድኑን ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከአማካዩ መስዑድ መሐመድ እና ኤልያስ አታሮ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል፤ እንዲህ አቅርበነዋል።
ኤልያስ አታሮ
ለተጋጣሚ ቡድን የሰጣችሁት ግምት አነስተኛ ነው?
እግርኳስ ነው ጨዋታው ማንንም ቡድን አቅልለን የምንመለከትበት ሁኔታ የለም። የትኛውም ቡድን በእግርኳስ የሚፈጥረው ነገር ቀድሞ መገመት አትችልም። የጅቡቲ ቡድን ወደ ዚህ ውድድር የገባው የሀገሩ ሊግ አሸናፊ በመሆን ስለሆነ የምንሰጠው ዝቅተኛ ግምት አይኖርም። የሚጫወተው በሜዳው መሆኑ ደግሞ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህ ከአምናው በተሻለ በጥሩ ሞራል ላይ እንገኛለን። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ራሳችንን በሚገባ አይተናል። እንዲሁም ከአዳማ ጋር በነበረው የሊጉ ጨዋታም ተሻሽለን በመቅረብ አሸንፈን አሁን በጥሩ ስሜት ላይ እንገኛለን።
ደሞዝ ባለመከፈሉ ምክንያት የተወሰነ ቀን ልምምድ አለመስራታቹ ተፅዕኖው አለው?
በቡድኑ ላይ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም። የተወሰኑ ቀናት ነው ልምምዶች ያልሰራነው፤ የነበረውን ችግር ከአመራሮቹ ጋር በመነጋገር ክፍተቱን አስተካክለናል። ያም ቢሆን የሊጉ መቋረጥ ፣ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጋችን የሚያሳድርብን ተፅዕኖ አለ። ያው ልምምዳችንን በተቀናጀ ሁኔታ አጠናቀን በመስራት የተሻለ ውጤት ይዘን እንመለሳለን።
ምን ያህል ርቀት ለመጓዝ አልማችኋል?
ቡድኑ የተሻለ ርቀት ይጓዛል ብዬ አስባለው። ምክንያቱም ታሪክ ለመስራት ሁሉም ፍላጎት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል። እንደ ቡድን በመጫወት የምናስበውን ረጅም ጉዞ እናሳካዋለን ብዬ አስባለው።
የቡድኑ ስብስብ አዲስ መሆኑስ?
ልክ ነው ከአምና የነበሩት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች አሁን ከቡድኑ ጋር የሉም። አዳዲስ ተጫዋቾች አሁን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለዋል። ልምድ ያላቸው በመሆናቸው ከነባሮቹ ጋር ለመቀናጀት ብዙም አላስቸገረንም። በምንችለው አቅም ክለባችንን በአፍሪካ መድረክ ላይ ደረጃውን ከፍ በማድረግ ደጋፊውን ለማስደሰት የምንችለውን እናደርጋለን።
መስዑድ መሐመድ
ለጨዋታው ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል?
ጥሩ እየሰራን ነው፤ በተለይ መርሐግብሩ ከወጣ ጀምሮ ለጨዋታው የተለየ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። ጅማ በነበረን ቆይታ አብዛኛውን የልምምድ ጊዜ ጨርሰን ነው የመጣነው። እዚህም ከመጣን በኋላ ቀለል ያሉ ለጨዋታ መዳረሻ ልምምዶችን እየሰራን እንገኛለን። ሁሉም ማለት ይቻላል በጥሩ የማሸነፍ ተነሳሽነት እና ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ከፈጣሪ ጋር በድል እንመለሳለን።
ስለ ተጋጣሚ ቡድናችሁ ምን ታስባላችሁ?
በተወሰነ መልኩ ለማየት ጥረት አድርገናል። ያም ቢሆን ማንም ይሁን ተጋጣሚያችን እኛ ባለን አቅም ኳስን መሠረት አድርገን በመጫወት ጠንካራ ቡድን ይዘን ለመቅረብ እየሰራን ነው ያለነው። የተጋጣሚ ቡድናችን ሁኔታ ብዙም አያሳስበንም።
ልምድህን ለቡድኑ ለማበርከት ምን ያህል ተዘጋጅተሀል?
የተጫዋቾቹ ህብረት እና አንድነት በጣም ጥሩ ነው። ተጫዋች ከተጫዋች ጋር ያለው ግኑኝነትም መልካም የሚባል ነው። የመጀመርያ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ተጫዋቾቹ አንድ ነገር ለመስራት ሁሉም ተነሳሽነት አላቸው። እኔም ሆንኩ ሌሎች ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ያለንን ልምድ ተጠቅመን ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን።