የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በመሆን በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 የውድድር ዘመን ተሳታፊ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ቴሌኮም ጋር በቅድመ ማጣርያው የመጀመረያ ጨዋታውን ማክሰኞ ጅቡቲ ላይ ያደርገል። የቡድኑን ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ጥያቄዎችን በመያዝ ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ ጋር የደረግነው አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
ስለ ቡድኑ ዝግጅት
ዝግጅት ጥሩ ነው። ለኢንተርናሽናል ጨዋታው ብቻም ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ውድድሮችም በቂ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። ቡድናችን ከአዳማ ከተማው ጨዋታ በኋላ ክፍተቶቹን በሚገባ እያስተካከለ ይገኛል። ለማክሰኞውም ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት እያደረግን የጨዋታውን ቀን እየተጠባበቅን እንገኛለን።
የተጫዋቾቹ ሁኔታ
ሁሉም በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ መጠነኛ የኢፌክሽን ችግር አጋጥሞት ይሄን ሁለት ቀን ልምምድ ከእኛ ጋር አልስራም። አሁን ከጉዳቱ እያገገመ በመሆኑ የህክምናው ባለሙያው ስላረጋገጠ አብሮን የሚጓዝ ይሆናል። በተረፈ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ሲገኙ ጨዋታውን አሸንፎ ለመመለስ ሁሉም ከፍተኛ በሆነ የማሸነፍ ተነሳሽነት ላይ ይገኛሉ።
ከደሞዝ ክፍያ ጋር በቂ ልምምድ አለመስራታቸው የሚፈጥረው ተፅዕኖ
አዎ ያው ልምምድ ሁልጊዜ ሲቋረጥ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው። ያም ቢሆን እንዳጋጣሚ ሆኖ እኛ ልምምድ ስናቋርጥ ሊጉም ተቋርጦ የነበረ መሆኑ በጣም ጠቅሞናል እንጂ ለቀናት ልጆች ልምምድ አቁመው ነበር። አሁን በከፊል ሁኔታዎች ተስተካክለው ባገኘናት አጭር ጊዜ ውስጥ በትክክልም ለዚህ ጨዋታ የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርገናል ብዬ ነው የማስበው።
ስለ ተጋጣሚያቸው
በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ አጫጭር ፊልሞችን ለመመልከት ሞክረናል። ሆኖም በአብዛኛው እኛ ትኩረት ያደረግነው የራሳችን አቅም እንዴት ነው የሚለው ላይ ነው። ተጫዋቾቼ ለጨዋታው የሚሆን ምን አቅም አላቸው የሚለውን ይዘን መሄዱ የተሻለ ስለሆነ ያተኮርነው ያለንን ብቃት በትክክል መተግበር እንዴት እንችላለን የሚለው ላይ ነው።
ለተጋጣሚያችን ምንም የምንሰጠው ዝቅተኛ ግምት የለም። እኛም ለውድድሩ አዲስ ነን፤ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍን ማሰብ እንጂ የምንሰጠው ዝቅተኛ ግምት የለም ። ውድድሩ ለክለቡም ሆነ ለእኔ አዲስ ነው። ስለዚህ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልጋለን። አሁን ለእኛ የሚያስፈልገን ግምት ሳይሆን ጨዋታውን ማሸነፍ ብቻ ነው። የቅርቡ የኢትዮጵያ እና ሶማልያ የመልስ ጨዋታ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል።
ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ልምምድ አለመስራታቸው
አዲስ አበባ ላይ ሰው ሰራሽ ሜዳ አግኝተን ብንዘጋጅ ጥሩ ነበር፤ ሆኖም ይህን ሜዳ አዲስ አበባ ማግኘት አልተቻለም። ሀዋሳ ለማድረግ ሞክረን ነበር፤ ቴክኒካል ጉዳዮች አጋጠሙንና ሳይሳካ ቀርቷል። ተጫዋቾቹም ቢሆን ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የመጫወት አቅም ስላላቸው በዚህ ረገድ የምንቸገር አይመስለኝም። እዛም ከደረስን በኃላ አንድ ቀንም ቢሆን በሜዳው ላይ ልምምድ የምናደርግ መሆኑ እና ኳስን መሠረት አድረገን የምንጫወት መሆናችን ብዙም አያስቸግረንም ብዬ አስባለው።