የሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ከዓርብ ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ሲያስተናግድ የቆየው የሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን ከ ወላይታ ድቻ አገናኝቶ በሀይቆቹ የ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማዎች የዛሬው ጨዋታ ሶስተኛ መርሀ ግብራቸው ሲሆን በሁለተኛው ሳምንት ወደ ጎንደር አምርተው በአፄዎቹ ከተረቱበት ስብስብ ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳን በተክለማርያም ሻንቆ፣ ምንተስኖት አበራን በፀጋዓብ ዮሴፍ በቅጣት ባልነበረው አምበሉ አዳነ ግርማ ምትክ እስራኤል እሸቱን በመጀመርያ አሰላለፍ ሲጠቀሙ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ድቻዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው ሳምንት ወደ ሽረ አምርተው ከሽረ ጋር ነጥብ ተጋርተው በወጡበት ጨዋታ ከተጠቀሙበት ስብስብ ውስጥ እሸቱ መናን በያሬድ ዳዊት፣ ተክሉ ታፈሰን በውብሸት ዓለማየሁ፣ አብዱልሰመድ ዓሊን በፀጋዬ አበራ፣ ባዬ ገዛኸኝን በአንዱዓለም ንጉሴ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በፌዴራል ዳኛ ቢኒያም ወርቃገኘው በተመራው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የተጠና የጨዋታ እንቅስቃሴን መመልከት ያልቻልንበት የኘበረ ቢሆንም ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ወደ ግብ በመድረስ ብልጫ የነበረው ሲሆን በወጣቱ አማካይ በረከት ወልዴ የሚመራው የድቻ አማካይ ክፍል ደግሞ ኳስ በመቆጣጠር የተሻለ የነበረበት ነው። 5ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በግራ የድቻ የግብ ክፍል ገብቶ ለእስራኤል የሰጠውን ኳስ እስራኤል ቢመታውም ታሪክ ጌትነት በአስደናቂ መልኩ ያወጣበት ኳስ የጨዋታው ቀዳሚ የግብ እድል ሲሆን ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ በኩል ሰጥቶት ታፈሰ ሰለሞን ያመከናት ኳስም በአስቆጪነቷ የምትጠቀስ ነበረች።
የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት ኃይል በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ቀሪ 20 ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ያለቀላቸው እድሎችን ቢፈጥሩም በወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ጥረት ሲከሽፉ ተስተውሏል። 35ኛው ደቂቃ ላይም የወላይታ ድቻ የግብ ክልል ውስጥ ተከላካዩ ኄኖክ አርፊጮ በአጥቂው እስራኤል እሸቱ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ታፈሰ ሰለሞን ባልተለመደ መልኩ ቄንጠኛ በሆነ አመታት አስቆጥሮ ሀይቆቹን ቀዳሚ አድርጓል።
ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ድቻዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ማግኘት የቻሉት በፍጥነት ነበር። ኄኖክ ኢሳይያስ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ተክለማርያም ቢመልሳትም የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ስህተት በታየበት መልኩ አርባምንጭ ከተማን ለቆ ድቻን የተቀላቀለው ጸጋዬ አበራ እግር ስር ገብታ ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑን አቻ በማድረግ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ውጤት ይዞ ለመውጣት በሚመስል መልኩ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት ጥረት አድርገዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አዲስዓለም ተስፋዬ የሞከረውና በ61ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ጋር ተገናኝቶ የሳተው፣ በመልሶ ማጥቃት 76ኛ ደቂቃ ደግሞ ፍቅረየሱስ ለእስራኤል ሰቶት እስራኤል በቀጥታ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት በሀዋሳ በኩል፤ በ73ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ በግራ በኩል ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ነፃ ቦታ ላይ የተላከለትን ኳስ ፊት ለፊት ከተክለማርያም ጋር ቢያገናኘውም ተክለማርያም በአስደናቂ ብቃት የመለሰበት በድቻ በኩል ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
በጨዋታው የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም አጥቅተው ቢጫወቱም የተሳካላቸው ሀይቆቹ ነበሩ። 84ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል ተቀይሮ ከገባ በኃላ ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ብሩክ በየነ ያሻማትን ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባሩ ገጭቶ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳ ከተማን አሸናፊ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታው ተጠናቆ 90+2 ላይ በጸጋዓብ ዮሴፍ በእረፍት ሰዓት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዲስ ፈራሚው አይቮሪኮስታዊው የግራ መስመር ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር በቸርነት ጉግሳ ላይ በሰራው አደገኛ አጨዋወት በቀጥታ ከሜዳ በቀይ ካርድ ተወግዷል። ጨዋታውም በሀይቆቹ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ተከታታይ ድልን አስመዝግቦ ከመሪዎቹ ተርታ ሲሰለፍ ወላይታ ድቻ በአንድ ነጥብ በዓመቱ ድል ካላስመዘገቡ ክለቦች አንዱ ሆኗል። አምስት ቢጫ ካርዶች እና አንድ ቀይ ካርድ በፌድራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው ሲመዘዙ አምና ወልድያ ከፋሲል በተደረገው ጨዋታ ከፍተኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ፌዴራል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ከህመሙ አገግሞ ዛሬ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን በ1ኛ ረዳት ዳኝነት መምራትም ችሏል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን በመጫን ያገኛሉ |