የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 2-1 ወላይታ ድቻ 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞችም ስለ ጨዋታው የሚከተለውን ብለዋል።

“በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ማስቆጠራችን አንድ ጥንካሬ እንዳለን ያሳያል ” – አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

የተሻለ ነገር ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየን ያለነው። ከፋሲል ያደረግነው ጨዋታ ላይም ጥሩ ነበርን። አሁን ደግሞ የተሻልን ነን፤ ግን ችግሮች አሉብን። በቀጣይ የምናስተካክላቸው በተለይ የአጨራረስ ችግራችን ክፍተቶችን እያየብን ነው። አጨራረሳችንን የማናስተካክል ከሆነ ለተቃራኒ ቡድን መነሳሳት ለኛ ክፍተትንም ይፈጥርብናል። ይህን ደግሞ እናስተካክላለን ብለን እናምናለን።

በተደጋጋሚ የቅብብሎች መቆራረጥ

የመቆራረጥ ችግር አይመስለኝም፤ እስከ መጨረሻው እንደርሳለን። ግብ አካባቢ ስንደርስ ግን የመፈፀም ችግር ነው፤ ውሳኔም የመስጠት ችግራችን ታይቷል። ከዕረፍት በፊት ሶስት አራት ኳሶች እያገኘን አምክነናል። እነሱ ኳሶች ቢገቡ ኖሮ ልጆቻችን የመነሳሳት ሂደቶች ይኖሩን ነበር። ተጋጣሚያችን ደግሞ አጨዋወቱን ይቀይር ነበር። ከመከላከል ወደ ማጥቃት ውስጥ ሲገባ ለኛ የበለጠ ክፍተት ይፈጥርብናል። ድቻዎች ደግሞ ይህንን መንገድ ዘግተውብናል። እሱም ሆኖ ግን ሰብረን ለመግባት ሞክረናል፤ ስንገባ ግን አባክነናል። እነዚህ ኳሶች ደግሞ እንዲያወርዱን አድርጎን ነበር። ቢሆንም ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ ጎል ማስቆጠራችን አንድ ጥንካሬ እንዳለን ያሳያል። 

” የአጨራረስ ችግር እየታየብን ነው ” ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

ከሞላ ጎደል ጨወታው ጥሩ ነበር። በሁለቱም በኩል የታየው ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር። በሚገባ እየሄድን ባለቀ ሰዓት ነው የገባብን። ለኔ የቅንጅት ችግር ይታያል ይህን ደግሞ በሂደት ሰርተን እናስተካክላለን፤ በመስራት ስለሚፈታ።

የመጨረሻ ኳሶች ላይ ውጤታማ ያለመሆን

ከአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጀምሮ እንዲህ አይነት ተደጋጋሚ ስህተቶችን በየቀኑ እየሰራን ነው። ነገር ግን አሁንም ሊቀረፍ አልቻለም። በቀጣይ ላለብን ጨዋታ ያንን ነገር አውጥተን ትኩረት አድርገን እንሰራለን። እስከ አሁን ድረስ የአጨራረስ ችግር ብዙ እየታየብን ነው። አሁንም የሚታየው የቅንጅት ችግር ብቻ ነው፤ ይህም የሆነበት ተጫዋቾቹ ከተለያየ ቦታ ስለመጡ እኔ እንደምፈልገው ለመሆን ጊዜያቶች ያስፈልጉናል። ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ከእለት ወደ እለትም መሻሻል አለ። አሁንም እንደምፈልገው ባይሆንም ግን ይሻሻላል፤ እናስተካክላለን።