በአራት ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፍ የቻለው መከላከያ የ2018/19 ቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ለማድረግ ነገ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ በነገው ዕለት ወደ ናይጄሪያ ይጓዛል።
የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው መሆኑን ተከትሎ የ2018/19 የቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳታፊ የሚሆነው መከላከያ በቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ከናይጄርያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር መመደቡ ይታወቃል።
ጦሩ በውድድር ዓመቱ ጅማሬ የሁለትዮሽ ዋንጫን በማሳካት በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። የ2011 የውድድር ዘመን የሊጉን የመጀመርያ ጨዋታውን ጥቅምት 25 ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን 2 – 1 መርታት ከቻለ በኋላ ምንም ዓይነት የነጥብ ጨዋታ ማድረግ ባይችልም ከሱዳኑ ክለብ አል ሂላል ኦቢያድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታን በማድረግ ዝግጅቱን በተጠናከረ ሁኔታ እየሰራ ቆይቷል።
በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚሰለጥነው መከላከያ በቡድኑ ውስጥ ምንም ዓይነት የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ነገ ማለዳ ላይ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ናይጄሪያ ያቀናል።
የ18 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ይሄን ይመስላል፡-
ግብጠባቂዎች፡ አቤል ማሞ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ
ተከላካዮች፡ ሽመልስ ተገኝ ፣ አዲሱ ተስፋዬ ፣ አበበ ጥላሁን ፣ ዓለምነህ ግርማ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ታፈሰ ሰርካ
አማካዮች፡ ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ አማኑኤል ተሾመ ፣ ፍሬው ሰለሞን ፣ ሳሙኤል ታዬ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ዳዊት ማሞ
አጥቂዎች፡ ተመስገን ገብረኪዳን ፣ ምንይሉ ወንድሙ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም
መከላከያ ከሬንጀርስ ጋር የሚያደርገውን የመጀመርያ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ የፊታችን ረቡዕ ኢኑጉ ላይ ያደርግና የመልሱን ጨዋታ በሳምንቱ ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያከናውናል። ይህን ዙር ካለፈም የአልጄርያው ቤል አቤስ እና የላይቤርያው ኤልአሲአር አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል፡፡