በ2010 ከተስፋው ቡድኑ ወደ ዋናው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በማደግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ዮሐንስ ዘገየ የተሻለ ልምድ እንዲያገኝ በማሰብ በውሰት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሰጥቷል።
ዮሀንስ በ2010 የውድድር ዘመን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ከቻለ በኋላ በተለይ የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ ባህር ዳር ከተማ ላይ በተዘጋጀው ውድድር ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ የመጫወት ዕድል ሰተውት በተከላካይ ስፍራ ላይ ለፈረሰኞቹ ዋና ቡድን መጫወት ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በ12 ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በመጫወት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርጓል። በተለይ ከአጨዋወት ባህርዩ በመነሳት በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዘንድ የደጉ ደበበ ምትክ እንደሚሆን እምነት ጥለውበት ቆይተዋል። አሁን ደግሞ በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲጫወት ለአንድ ዓመት ውሰት የተሰጠ ሲሆን ያለፉትን 15 ቀናት ከኤሌትሪኮች ጋር ልምምድ እየሰራ ቆይቷል። የወረቀት ጉዳይ በዚህ ሳምንት አልቆለት የኢትዮ ኤሌትሪክን የመጀመርያ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታን በሚያደርግበት ጊዜ ይጫወታል ተብሎም ይጠበቃል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ዓመት ብቻ ከተስፋ ቡድን ካሳደጋቸው ተጫዋቾች መካከል ተስፋዬ በቀለ እና አቤል አምበሴ ጋር የተለያየ ሲሆን ዮሐንስ ዘገየ በውሰት ወደ ሌላ ክለብ የተሰጠ ተጫዋቾች ነው። በሌላ ዜና ደግሞ ከተስፋ ቡድን ያደገው እንዲሁም ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግራ ተከላካይ መስመር የተጫወተው ሳሙኤል ተስፋዬ ከፈረሰኞቹ ጋር ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት በቅርቡ ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።