ሳላዲን ፣ ኡመድ እና ጌታነህ ከሳኦቶሜው ጨዋታ ውጪ ሆኑ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ለሚያደርገው የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ በመጪው ማክሰኞ በጋና አድርጎ ወደ ሳኦቶሜ ያቀናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከቦትዋስና ጋር ካደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ በኋላ ተጫዋቾቹ ያልተበተኑ ሲሆን የዛሬው የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ አድርገው የሚመለሱ ተጫዋቾችን ጨምሮ ከውጭ ሃገር የሚመጡት ዋሊድ አታ እና ሽመልስ በቀለ ወደ ስፍራው ያቀናሉ ተብሏል፡፡ዋሊድ ማክሰኞ አዲስ አበባ ገብቶ ከቡድኑ ጋር ይጓዛል ተብሎ ሲጠበቅ ሁኔታዎች በታቀዱበት ጊዜያት ካልተከናወኑ ለብቻው ወደ ሳኦቶሜ በማቅናት ለጨዋታው ይደርሳል ተብሏል፡፡ የፔትሮጄቱ ኮከብ ሽመልስ በቀለ ማክሰኞ ጠዋት አዲስ አበባ በመግባት ከቡድኑ ጋር አብሮ ይጓዛል ተብሏል፡፡

የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት አምበሉ ሳላዲን ሰኢድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ኡመድ ኡኩሪ ሳኦቶሜን ለመግጠም በሚጓዘው ቡድን ውስጥ አልተካተቱም፡፡ እንደ አቶ ወንድምኩን ገለፃ ሶስቱ ተጫዋቾች የተቀነሱት በአስጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ውሳኔ ነው፡፡ ሳላዲን ሰኢድ በቅርብ ሳምንታት ለኤምሲ አልጀር በቂ ጨዋታዎችን ማድረግ አልቻለም፡፡ እስካሁን ሙሉ ጨዋታ ያልተሰለፈ ሲሆን የመጨረሻዎቹን 2 ጨዋታዎች ከተጠባባቂ ወንበር ሳይነሳ ጨርሷል፡፡ ጌታነህ ከበደ በውሰት በሚገኝበት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያ የተሸለ የመጫወት እድል ቢያገኝም ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ ኡመድ ኡኩሪ ደግሞ በአዲሱ ክለቡ ኢ.ኤን.ፒ.ፒ.አይ ጨዋታ አላደረገም፡፡ የተጫዋቾቹ ወቅታዊ አቋም መልካም አለመሆን አሰልጣኝ ዮሃንስ ይህንን ውሳኔ እንዲወስኑ በር መክፈቱ ቢገመትም አሰልጣኙ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በቋሚ አሰላለፋቸው ውስጥ ከማካተት ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጣቸው የሚታወስ ነው፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ወደ ቦትስዋና ይዘዋቸው ከሄዷቸው 19 ተጫዋቾች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ዋንጫ መልካም አቋም ያሳዩት የመከላከያዎቹ በኃይሉ ግርማ ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና ምንይሉ ወንድሙን ወደ ቡድናቸው የቀላቀሉ ሲሆን ዛሬ 6 ተጫዋቾችን በመቀነስና ዋሊድ እና ሽመልስን በማካተት በአጠቃላይ 18 ተጫዋቾችን (አጠቃላይ 26 የልኡካን ቡድን) ማክሰኞ የሳኦቶሜ ጉዟቸውን ይጀምራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው ሀሙስ መስከረም 27 ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የአለም ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ሰኞ ጥቅምት 1 በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል፡፡

ያጋሩ