መከላከያ በካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ የ2018/19 የውድድር ዓመት ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከናይጄሪያው ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል ጋር ኢኑጉ ላይ ረቡዕ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል። ነገ ወደ ስፍራው የሚያቀኑት መከላከያዎች ስላደረጉት ዝግጅት እና ተዛማጅ ጉዳዮች የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑት አምበሉ ሽመልስ ተገኝ እና አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ እንዲህ አቅርበነዋል።
ሽመልስ ተገኝ
ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል
የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ከሆንን በኋላ ስለ ኢንተርናሽናል ጨዋታው ነው አሰበን እየተዘጋጀን ያለነው። ከዚህ በፊት አንድ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ተጫውተን በድል አጠናቀናል። አሁን ሙሉ ትኩረታችን ለሬንጀርሱ ጨዋታ ነው። እንደሚታወቀው ለዚህ ውድድር አዲስ አይደለንም፤ በተለያዩ ዓመታት ረጅም እርቀት ባንጓዝም ተሳትፈን እናውቃለን። አሁን ከዚህ ቀደም የነበሩብንን ክፍተቶች አርመን ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራን እንገኛለን። የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለው።
ከሌሎቹ ዓመታት ምን የተለየ ነገር እንጠብቅ
መከላከያ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጉዞ አንድ ሁለት ደረጃ ከፍ እንዲል ለማድረግ እኛ ጠንክረን እየሰራን ነው። በአመራር በኩልም የተሻለ ውጤት እንድናስመዘግብ ከፍተኛ ድጋፍ ነው እያደረጉልን የሚገኙት። አሰልጣኞቻችንም ቢሆን ጥሩ ነገር እየሰጡን፣ እያበረታቱን እስካሁን ውጤታማ ጉዞ እያደረግን ነው የምንገኘው። ከዚህ ቀደም ከነበረው ዝቅተኛ ጉዟችን የተሻለ ውጤት ዘንድሮ ለማስመዝገብ አስበናል።
የምዕራፍ አፍሪካ ቡድኖች የተለመደ አጨዋወትን ለማቆም ምን ታስባላቹ?
ተጨማሪ የአንድ ሰአት ቪዲዮችን አይተናል። የእነሱን አጨዋወት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየሰራን ነው። በእርግጥ የቆሙ ኳሶች ወይም መስመር ላይ ያመዘነ አጨዋወት እንደሚከተሉ ቢታወቅም እኛ ደግሞ ኳሱን ተቆጣጥረን እግራችን ላይ ባለማቆየት ጥሩ ስራ ሰርተን ውጤት አስጠብቀን እንመለሳለን።
የመጀመርያው ጨዋታ ከሜዳ ውጪ መሆኑ ጠቀሜታው ምን ድረስ ነው?
ወደ ሜዳ ስትገባ ሁሌም ማንኛውም ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምትገባው። በእግርኳስ ስሌት ከሄድን ከሜዳ ውጭ መጫወታችን አቻም ቢሆን ያዋጣናል። ያም ቢሆን ግን ከቻልን አሸንፎ በድል መመለስ ደስታችን ነው። ካልቻልን ግን ለመልሱ ጨዋታ የሚረዳን ውጤት ይዘን እንመለሳለን።
ምንይሉ ወንድሙ
ለጨዋታው ያላቹ ዝግጅት?
ከፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ በኋላ ይኸው ያለፉትን አስር ቀናት ካምፕ በመግባት ለጨዋታው የተለየ ዝግጅት እያደረግን ቆይተናል። ከዚህ ቀደሙ የተሻለ አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ውጤት ለማግኘት እየሰራን ነው። የተጫዋቾቹም ለጨዋታው ያላቸው ተነሳሽነት በጣም ጥሩ ነው። አሸንፎ ለመመለስ ነው የምናስበው። እኔም በግሌ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምዴን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በምችለው አቅም ቡድኑን ለማገዝ ጠንክሬ እየሰራው ነው።
ስለ ተጋጣሚያቹ ምን ትላለህ?
ለአንድ ሰዓት የቆየ ፊልሞችን አይተናል። ኳስን መሰረት አድርገው የሚጫወት ቡድን መሆኑን አይተናል። የምንጫወትበት ሜዳ ሰው ሰራሽ በመሆኑ የበለጠ መጫወት የፈለግነውን አጨዋወት ለመተግበር ይረዳናል። እኛ ከእነርሱ የተሻለ ሆነን በመቅረብ ጥሩ ውጤት አስመዝግበን እንመለሳለን።