በኮፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከናይጄሪያው ሬንጀርስ ረቡዕ የሚያደርገው መከላከያ ነገ ወደ ስፍራው ያቀናል። ክለቡ ለጨዋታው ባደረገው ዝግጅት ዙርያ ጥያቄዎችን በመያዝ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን አናግረን እንዲህ አቅርበነዋል።
የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ምን ይመስላል?
ከጥቅምት 25 የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታችን በኋላ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታችን ያደረግነው በኮፌዴሬሽን ዋንጫ ላለብን ወሳኝ ጨዋታ ነው። በዝግጅታችንም ወቅት ከሱዳኑ አል ሂላል ኦቢዬድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ችለናል። በዚህ ወቅት አምስት ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ሄደውብን የነበረ ቢሆንም አሁን አብረውኝ ነው ያሉት። ተጫዋቾቼ በሚገባ ስሜቴን ስለሚጋሩ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ አንድነት እና ቅንጅት እየፈጠርንም በመሆኑ መልካም ነገር ያጋጥመናል ብዬ አስባለው።
መከላከያ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ርቀት ይጓዝ ይሆን?
መከላከያ የኢትዮጵያን ዋንጫ አሸናፊ ይሁን እንጂ በኢንተርናሽናል መድረክ ከቅድመ ማጣርያ ከአንድ በላይ የተሻገረበት ታሪክ የለውም። አሁን ሁላችንም እየሰራን የምንገኘው በዚህ ወቅት ያለነው ትውልድ የተሻለ ነገር ለማድረግ እና ያለፈውን ታሪክ ለመቀየር ነው። በእርግጥ ተጋጣሚዎቻችን ጥሩ አቋም ያላቸው ቢሆኑም እኛም እያደረግን ያለነው መልካም ነገር ስለሆነ ያለፈውን ታሪክ ለመቀየር የሚያስፈልገውን ሁሉ እየሰራን ነው የምንገኛው።
ተጋጣሚያችሁን የማየት አጋጣሚ አግኝተዋል?
ሬንጀርስ ጥሩ ቡድን ነው። የ60 ደቂቃ ቪዲዩ አግኝቼ እንቅስቃሴውን ለማየት እንደቻልኩት ከተለመደው የምዕራፍ አፍሪካ ቡድኖች የተለየ አጨዋወት ነው የሚከተሉት። ምንም እንኳን በሰውነታቸው የገዘፈ የአካል ብቃት ቢኖራቸውም እንደኛ ኳስን መሰረት አድርገው፣ ኳስን ይዘው ለመጫወት የሚሞክሩ ናቸው። ከእኛ አጨዋወት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ አንድ አይነት አቅም ያለን ይመስለኛል። ዛሬ ከቡድኑ ተጫዋቾቼ ጋር በመሆን ፊልሙን እናየውና አጨዋወታቸው ምን እንደሚመሰል እናያለን። በነገራችን ላይ የምንጫወትበት ሜዳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ ኳስን ለሚጫወት ቡድን የማሸነፍ እድሉ የሰፋ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በተሻለ በልጠውን እንዳይገኙ እኛ ባለን ነገር ላይ የተሻለ ነገር ጨምረን ውጤቱን ይዘን ለመመለስ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል። ቁም ነገሩ ሜዳ ላይ ትልቅ የሆነ ቡድን አሸንፎ ይወጣል።
መከላከያ በሀገር ውስጥ ተጫዋች ብቻ የተዋቀረ ቡድን ነው። በኢንተርናሽናል መድረክ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች አለመኖር እንድምታን እንዴት ያዩታል?
በእርግጥ የውጭ ተጫዋች ሲባል ከእኛ በጣም የገዘፉ እና የተሻሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። እኛን የሚያስተምሩ በቡድኑ ውስጥ ልዩነት የሚፈጥሩ ቢሆኑ በቡድኑ ውስጥ ቢኖሩ ይመረጣል፤ ምንም አይደለም። ነገር ግን እኛ ደግሞ ሀገር ውስጥ ካሉት ጋር ተጫዋቾች በጣም ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑ ተጫዋቾች ነው የያዝነው። የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ይዘን በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ጥሩ ነገር ይዘን ብንጓዝ ለእኛ ጥሩ ነው። ከእነዚህ የሚወጣ ነው ነገ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚጫወቱት። ስለዚህ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ መሆኑ ጥሩ መለመድ ያለበት ነገር ይመስለኛል።
ከሜዳ ውጭ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች?
በማንኛውም ጊዜ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሀገር ስትሄድ አልፎ አልፎም ወደ ሰሜን አፍሪካም ስትሄድ የሜዳ ተጠቃሚነትን በምንም አይነት መንገድ ይሁን ውጤቱን መውሰድ ፍላጎት አላቸው። አሁን ሬንጀርስ በሜዳው የመጀመርያውን ጨዋታ ተጫውቶ የመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ ስቴዲየም በአየር ሁኔታ ይሁን በሜዳው አለመመቸት እንደሚቸገር ስለሚያውቀው ነገሮችን ሁሉ እዛው መጨረስ ነው የሚፈልጉት። ለዚህም የተለያዩ ነገሮች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ እንገምታለን። እኛም ወደ እዛ ስንጓዝ ይህ ሊያጋጥም እንደሚችል ተዘጋጅተን ነው የምንሄደው።