ሁለቱ ኢትዮጵውያን የሚገኙባቸው ክለቦች ፔትሮጀት እና ስሞሃን ያገናኘው ጨዋታ በፔትሮጀት አሸናፊነት ተጠናቋል። ሽመልስ በቀለ በጨዋታው ደምቆ ቢያመሽም በመጨረሻ ደቂቃ የሁለት ቢጫ ሰለባ ሆኗል።
12 : 15 በጀመረው እና ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ፔትሮጀቶች በፈጣን እንቅስቃሴ የተሻለ የጎል እድል ሲፈጥሩ በ13ኛው ደቂቃም ላይ ጎል አስቆጥረዋል። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሽመልስ በቀለ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለት ኳስ መሐመድ ሳላህ ወደ ግብነት ቀይሮ ፔትሮጀቶችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው የቡድኑን የአጥቂ መስመር በብቸኝነት የመራው ሽመልስ በመጀመርያው ደቂቃዎች በርካታ የጎል እድሎች ሲፈጥር ሁለት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርጓል። በተለይ ከቅጣት ምት ያረጋት ሙከራ እና መሐመድ ቬራ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያልተጠቀመባት እድል ለጎልነት የቀረቡ ነበሩ።
በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት እንግዶቹ ስሞሃዎች እጅግ በርካታ የጎል እድሎች አምክነዋል። በተለይም ሺሎንጎ ያመከናት እና ያስር ኢብራሂም በግንባሩ ገጭቶ ያደረጓቸው ሙከራዎች እጅግ አስቆጪ ነበሩ። ከነዚ ሙከራዎች ውጭም በ39ኛው ደቂቃ ላይ መሃመድ ሓምድ ዛዚ ያመከናት ወርቃማ አጋጣሚም እንግዶቹን አቻ ለማረግ ከተቃረቡ ሙከራዎች አንዷ ናት። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የስሞሃ የአሰልጣኞች ቡድን ከዳኞቹ ጋር የፈጠሩት ለደቂቃዎች የቆየ እሰጣ ገባም ሌላው በጨዋታው የታየ ክስተት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ስሞሃዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይ ከመሆናቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ወደ ፔትሮጀት የግብ ክልል ተጠግተው በርካታ የግብ እድሎች ሲፈጥሩ ባለሜዳዎቹ በመከላከል ተጠምደው ነበር። አይቮሪኮስታዊው ያማዶ ቱሬ ባመከናት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ስሞሃዎች በሺሎንጎ እና ያማዶ ቱሬ እና መሃመድ ሃምድ ዛኪ በርካታ የጎል እድሎች ቢፈጥሩም የአቻነት ጎል ማግኘት አልቻሉም።
ከመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት ሲታይ ተዳክመው የታዩት ፔትሮጀቶች ሽመልስ በቀለ እና መሐመድ ቬራ በግላቸው ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውጭ ሙሉ በሙሉ በመከላከሉ ላይ አተኩረው ተጫውተዋል። ሆኖም በሁለቱ ተጫዋቾች አማካኝነት ጥቂት የማይባሉ የጎል እድሎች ፈጥረዋል። ቬራ አሻግሮለት ሽመልስ ያልተጠቀመበት እና ሽመልስ ያቀበለው ኳስ ተጠቅሞ ቬራ መቶ ግብጠባቂው ያዳነበት በፔትሮጀት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው። የአቻነት ጎል ለማግኘት አጥቅተው የተጫወቱት ስሞሃዎችም እድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም ዑመድ ኡክሪ ከመስመር የተሻማችለትን ኳስ በግምባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።
በጨዋታው 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ተቀይሮ በሚወጣበት ሰዓት ከአይቮሪኮስታዊው ያማዶ ቱሬ ጋር በፈጠረው እሰጣ ገባ በሁለት ቢጫ (ቀይ ካርድ) ከሜዳ ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎ የሞማን ሶሊማኑ ፔትሮጀት ተከታታይ ድል አስመዝግቦ ከወራጅ ቀጠና በመውጣት 14ኛ ደረጃን ሲይዝ ስሞሃ አሁንም ለተከታታይ አምስተኛ ሳምንት ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ተስኖታል።