አርቢቴር ጌቱ ተፈራ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

በኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ የ2ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ የተደረገውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመራው ፌዴራል አርቢቴር ጌቱ ተፈራ በጨዋታው የዳኝነት ስህተት ፈፅሟል በሚል የ18 ወራት እገዳ ውሳኔ ተላልፎበታል።

በፋሲል ከነማ 3-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታ በአቻ ውጤት ቀጥሎ ባለበት ሰዓት በ87ኛው ደቂቃ የወሰኑት ውሳኔ ጨዋታውን ለ20 ደቂቃዎች እስከማስተጓጎል ያደረሰ ነበር። ለፋሲል ከነማ የፍፁም ቅጣት ምት በሰጡ ቅጽበት ውሳኔውነረ በመሻር ክስተቱ በፊት የተቆጠረውን ጎል ሲያፀድቁ ኋላ ላይ ደግሞ በድጋሚ ውሳኔያቸውን በመቀየር የፍፁም ቅጣት ምት እንዲመታ አድርገው አዳነ ግርማን ከሀዋሳ በኩል በቀይ ካርድ ማስወጣታቸው ይታወሳል። በዚህ ዙርያ የፌዴሬሽኑ ዳኞች ኮሚቴ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።


የፌዴሬሽኑ የቅጣት ውሳኔ ይህንን ይመስላል:-

በኢትዮጵያ ወንዶች ኘሪምየ ር ሊግ የ2011 ዓ.ም የ 2ኛ ሳምን ት ጨዋታ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም መርሃ ግብር በጎንደር ስታዲየ ም በፋሲል ከተማና በሐዋሳ ከተማ ክለቦች መካከል በተካሄደ ጨዋታ ላይ የጨዋታው ዋና ዳኛ በነበሩት ፌደራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራን አስመልክቶ የጨዋታው ታዛቢ (ኮሚሽነር) ባቀረቡት የአፈጻፀም ሪፖርት እንዲሁም ዋና ዳኛው ጨዋታውን በመሩት ወቅት ስለፈፀሙት የቴክኒክ ስህተት ያቀረቡትን የይቅርታ ደብዳቤ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥልቀትና በስፋት ከተወያየ በኋላ፣

1ኛ. ፌዴራል ዋና ዳኛ ጌቱ ተፈራ የፈፀሙት ከፍተኛ የቴክኒክ ስህተት ከአንድ ሲኒየር ፌዴራል የእግር ኳስ ዳኛ የማይጠበቅ ጥፋት መሆኑን በማስታወስ፣

2ኛ. በፌዴራል ዳኛነት ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሚያስቀጣ ስህተት ፈጽመው የማያውቁና ባሳዩት የአፈፃፀም መሻሻል በኤሊት ዳኛነት ውስጥ መግባታቸውን እንዲሁም አስከዚህ ጨዋታ ድረስ የነበራቸውን መልካም አፈፃፀም ከግምት በማስገባት፣

3ኛ. ከጨዋታ ፍጻሜም በኋላ ስለፈፀሙት የቴክኒክ ስህተት በማመንና ለወደፊት ከዚህ ዓይነት ድርጊት ተቆጥበው የሚመደቡበትን ጨዋታ በአግባቡና በትክክል ለመምራት የሚዘጋጁ መሆናቸውን በጽሑፍ በማረጋገጣቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ ዳኞች፣ ኢንስትራክተሮችና ታዛቢዎች የሥነ-ስርዓት እርምጃ ደንብ ክፍል 3 አንቀጽ 6 ተራ ቁጥር 6.8.2 እና 6.9 መሠረት ለ1 ዓመት ከ6 ወር ከእግር ኳስ ዳኝነት እንዲታገዱ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡


ጌቱ ተፈራ ከዚህ ቀደም በ2008 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ውድድር ላይ የስነ-ምግባር ጥሰት ፈፅሟል በሚል እገዳ ተላልፎበት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በ2010 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ያደረጉትን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የመራበት መንገድ ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡