የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 የውድድር ዓመት የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ከትላንት ጀምሮ መካሄድ ሲጀምሩ ከጅማ አባጅፋር በተጨማሪ ኢንተርናሽናል ዳኞቻችንም ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛል።
ከቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የኬንያው ጎር ማሂያ እና የማላዊው ንያሳ ቢግ ቡሌትስ የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ ተካሂዶ ጎር ማሂያ 1-0 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን የመልስ ጨዋታው በቀጣዩ ረቡዕ ማላዊ ብላንታየር ከተማ ላይ ይከናወናል። ይህን ጨዋታም ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ሲመራው በላቸው ይታየው እና ሽዋንግዛው ተባባል በረዳትነት አብረውት ይመራሉ። ብሩክ የማነብርሀን ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት መመደቡ ታውቋል።
በ2018 የፊፋ ባጅ ያገኘው ቴዎድሮስ ከሳምንት በፊት የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ ሲሸልስ ከሱዳን ያደረጉትን ጨዋታ መዳኘት የቻለ ሲሆን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ሲመራ የመጀመርያው ነው።
ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በአፍሪካ ውድድሮች በተደጋጋሚ የመምራት እድል እየተሰጣቸው ይገኛል። በዚህ ወር ብቻም የ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ፣ የቻምየንስ ሊግ ፍፃሜ፣ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ (መክፈቻ እና ግማሽ ፍጻሜ) እንዲሁም የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያዎች በኢትዮጵያውያን ዳኞች ተመርቷል።