-በፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ተጫዋቾቹን ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ተጫዋቾቹ ልምምድ አቁመዋል።
የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከቅርብ ጊዚያቶች ወዲህ በገጠመው ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት በርካታ ውጣ ውረድ አልፎ በዚ ውድድር ዓመት መሳተፉ እርግጥ ሆኖ የነበረ ቢሆንም አሁንም ችግሩ በዘለቄታዊነት መፈታት ባለመቻሉ የተጫዋቾች ደሞዝ መክፈል አቅቶት ክለቡ በችግር እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸው የሰጡን የቡድኑ ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም አበራ ችግሩ ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች ማድረጋቸው ገልፀው ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገቡት አጋር ድርጅቶች ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታቸው የተጫዋቾቻቸው ደሞዝ ለመክፈል እንደተቸገሩ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ችግሩ በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳረፈ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኤፍሬም የአጋር ድርጅቶቹን ምላሽ የዘገየበት ምክንያትም እንደማያውቁም ገልፀውልናል። ” እኛ ችግሩ ለመፍታት የተቻለን እያደረግን ነው። እስካሁን ድረስ ያካሄድናቸውን ጨዋታዎችም በጫና ውስጥ ሆነን ነው ያደረግናቸው። ችግሩ በቡድናችን ውጤት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ነው” ብለዋል።
በሊጉ ሦስቱንም ጨዋታዎች አከናውኖ ሁሉንም የተሸነፈው ደደቢት ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በደቡብ ፖሊስ ከተሸነፈበት ጨዋታ በፊትም የልምምድ ቁሳቁሶች እና ኳሶች በተውሶ ሲጠቀም ተስተውሏል።