ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ እና ጥረት ሲያሸንፉ ሀዋሳ ከአዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ጥረት አሸንፈዋል። የተጠበቀው የአዳማ እና ሀዋሳ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ


በዳዊት ጸኃዬ

አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ ፍፁም የበላይነት 3-0 ተጠናቋል።

ወደ መስመር ባደላ መልኩ በፍጥነት ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ የነበሩት ባንኮች የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው 6 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ረሂማ ዘርጋው ከረጅም ርቀት አክርራ በመምታት ቀዳሚ ያደረገቻቸውን ግሩም ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ በደቂቃዎች ልዩነትም በቀኝ መስመር በኩል ሰብረው የገቡትን ኳስ ሽታዬ ሲሳይ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ሞክራ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ልትወጣ ችላለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች እምብዛም ባንክን መፎካከር ባልቻሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ በ23ኛው ደቂቃ ዳግማዊት ሰለሞን ከሳጥን ውጭ አክርረ መታ ፍሬወይኒ ገብሩ ያዳነችባት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡ በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥር ድርሻ የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም የጠሩ የግብ እድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ከረመም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሰናይት ባሩዳ አክርራ በመምታት ወደ ግብ የላከችው ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊሷ ግብጠባቂ ከምባቴ ኪቲላ ስህተት ታግዛ ከመረብ ተዋህዳለች። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በንግድ ባንክ የ2ለ0 የበላይነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑም ቢሆን መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ ንግድ ባንኮች ተጫዋቾችን ለመሞከር በሚመሰል መልኩ ተመሳሳይ ሚና መወጣት የሚችሉ ተጫዋቾችን በመተካት የመጫወቻ ደቂቃ እንዲያገኙ እድል ሲፈጥሩ በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ወደ ኃላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። ይህም ለንግድ ባንኮች የሁለተኛው አጋማሽ የመሀል ሜዳ የበላይነት አይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

እምብዛም የግብ መከራዎች ባልታየበት የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ ንግድ ባንኮች በ90+2ኛው ደቂቃ ላይ በሽታዬ ሲሳይ ተጨማሪ ሶስተኛ ግብን አስቆጥረው ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ3ለ0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዚህም ንግድ ባንክ ከሁለት ጨዋታዎች 6 ነጥብ በመሰብሰብ ሊጉን ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡


አዳማ ከተማ 1-1 ሀዋሳ ከተማ


በዳንኤል መስፍን

አዳማ ላይ ከሳምንቱ ጨዋታዎች ክብደት የተሰጠው የአዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ተካሂዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በፈጣን እና በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ አዳማ ከተማዎች ተሽለው የጀመሩ ሲሆን በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ወደ ጎል አክርራ የመታችውን ኳስ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ዓባይነሽ እንደምንም ስትመልሰው በቅርብ ርቀት የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ወደ ጎልነት ቀይራው ባለሜዳዎቹ አዳማ ከነማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

በዳኞቹ እርስ በእርስ ያለመናበብ የተነሳ ተደጋጋሚ ያልተገባ ፊሽካ በመንፋት የጨዋታውን ፍጥነት እያቆራረጡት ቢያቀዛቅዙትም አዳማዎች እንደወሰዱት ብልጫ እና እንደ ሀዋሳ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ደካማነት ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር። በሀዋሳ በኩል አጥቂዋ ምርቃት ፈለቀ እና አዲስ ፈራሚዋ አማካይ ወርቅነሽ መሰለ በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት እና መልካም እንቅስቃሴ ውጭ በተደራጀ መልኩ ጎል የማስቆጠርም ሆነ ለጎል የቀረበ የተሳካ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው የመጀመርያውም አጋማሽ በዚህ መልክ በአዳማ መሪነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ዮሴፍ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ በቡድኑ ውስጥ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉትን ተጫዋቾችን በፍጥነት በመቀየር ይዘውት የገቡት የጨዋታ አቀራረብ ሲረዳቸው በአንፃሩ አዳማዎች ተዳክመው ቀርበዋል። 54ኛው ደቂቃም ላይ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ ወደ ጎል የመታችውን ኳስ ተደጋጋሚ ቀላል የሆኑ ስህተቶችን ትሰራ የነበረችው የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ስትተፋው ቅድስት ዘለቀ ወደ ጎልነት ቀይራው ሀዋሳዎችን ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት ሀዋሳዎች በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ በዋለችው ምርቃት ፈለቀ አማካኝነት ጫና ፈጥረው ከመጫወት በዘለለ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። የሜዳውን ቀኝ መስመር ላይ ብቻ ባደላ ሌሎቹን የሜዳ ክፍሎችን ዘንግቶ በቀሩት ደቂቃዎች የቀጠለው ጨዋታ ምንም የረባ እንቅስቃሴ ለጎል የቀረበ ሙከራ ሳናይበት 1 – 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።


ጥረት ኮርፖሬት 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

 

በሚካኤል ለገሰ

ባህር ዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አግኝቷል። ሁለት መልኮች በተስተዋሉበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ጥረት ኮርፖሬቶች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ተጋባዦቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ብልጫ ወስደው ተንቀሳቅሰዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በ6ኛው ደቂቃ በኤሌክትሪክ አማካኝነት ሲደረግ ቤተልሄም ከፍያለው ለአይናለም ፀጋዬ ያቀበለቻትን ኳስ ቤተልሄም ኳሷን በግንባሯ ወደ ጎልነት ለመቀየር ሞክራ ሳይሳካላት ቀርቷል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ የሰጡት ጥረቶች በቁምነገር ካሳ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው አምክነዋል። ከዚች ሙከራ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያልተቸገሩት ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ላይ ደርሰው ሙከራዎችን ሲያደርጉ ታይቷል። በ13ኛው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ብቃቷን ስታሳይ የነበረችው ምስር አብርሀም ቡድኗ በጊዜ መሪ ሊሆን የሚያስችለውን የግብ አጋጣሚ አግኝታ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ተረባርበው አምክነውባታል። ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ጥረቶች ከቆሙ ኳሶች (ከማዕዘን እና ከቅጣት ምት) ግቦችን ለማስቆጠር ሞክረው በ41ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸዋል። አዲስ ንጉሴ በ41ኛው ደቂቃ ራሷ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ ራሷ በግንባሯ ወደ ግብነት ቀይራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መነቃቃቶችን ያሳዩት ኤሌክትሪኮች የመጀመሪያው አጋማሽ ሳይጠናቀቅ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ጥረቶች ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎችን በትመር ጠንክር አማካኝነት ያደረጉ ሲሆን አንደኛውን ግብ ጠባቂዋ እስራኤል ከተማ አንደኛውን ደግሞ የግቡ ቋሚ አምክኖታል። ከግቡ በተጨማሪ እነዚህ ሁለት አስደንጋጭ ሙከራዎች ያነቃቸው የሚመስሉት ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ ለመድረስ ቢጥሩም የተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ጋር ሲደርሱ በሚፈጥሩት የውሳኔ ስህተት ፍሬ ለማፍራት ሲቸገሩ ተስተውሏል። ይህንን ለመቅረፍ አሰልጣኝ እየሩሳሌም በርካታ የአጥቂ እና የመስመር ተጨዋቾችን ቀይራ ብታስገባም ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል።

በአሰልጣኝ ሰርካዲስ የሚመሩት ጥረቶች ደግሞ መሪነታቸውን አሳልፎ ላለመስጠት ወደ ኋላ አፈግፍገው ነገር ግን አንዳንድ ግልፅ እድሎች ሲገኙ በቀጥተኛ አጨዋወት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በ80ኛው ደቂቃም ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችው ኪዳን ጌትነት አማካኝነት ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ኪዳን የመታችው ኳስ ኢላማዋን በመሳቷ ኳስ እና መረብ ሳይገናኙ ቀርተዋል። 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት ኤሌክትሪኮች ያለቀለት የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ዓለምነሽ ገረመው እድሉን አምክና ጨዋታው በጥረት 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ውጤቶች እና ቀጣይ ጨዋታዎች፣ የደረጃ ሰንጠረዥ እንዲሁም እስካሁን ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች:-

2ኛ ሳምንት
እሁድ ኅዳር 16 ቀን 2011
መከላከያ 3-2 ድሬዳዋ ከተማ
ቅዳሜ ኅዳር 22 ቀን 2011
አዳማ ከተማ 1-1 ሀዋሳ ከተማ
ጥረት ኮርፖሬት 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮ ንግድ ባንክ 3-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ
እሁድ ኅዳር 23 ቀን 2011
ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 09:00 አዲስ አበባ ከተማ
አርባምንጭ ከተማ 09:00 ጌዴኦ ዲላ